
መስከረም ሲጠባ አዲስ ዓመት ሲገባ ወደ ልጅነት ዓለም በትዝታ መመለስ የተለመደ ነው። ምድር በአበባ ስትዋብ፤ ልምላሜ በምድር ላይ ሲነግስ የተማሪዎች ተስፋ እና ጉጉት እውን መኾን ይጀምራል።
በሰኔ የተለያዩ ጓደኞች በመስከረም ለመገናኘት ይጓጓሉ። የትምህርት ምዝገባ አልቆ፤ የትምህርት ቁሳቁስ ተገዝቶ፤ የደብተር ቦርሳ የተገዛለት በቦርሳው፤ ያልተገዛለት ደግሞ ከተለያዩ ቁሳቁሶች ቦርሳ በመሥራት ለትምህርት ይዘጋጃሉ።
ትምህርት ሲጀመር የተነፋፈቁ በፍቅር ይተቃቀፋሉ፤ በትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ በሳር ላይ ይራወጣሉ፤ ጠመኔን በናፈቁ ሰሌዳዎች ላይ ተስፋቸውን በትልቁ ይጽፋሉ፤ የናፈቋቸውን መምህራን በደስታ ያቅፋሉ፤ የዓመቱን ትምህርት በውጤታማነት ለማጠናቀቅ የመልካም ፉክክሩን መጀመርን ይፋ ያደርጋሉ።
ሕጻናት እንደ አደይ አበባ በማለዳ ይፈካሉ፤ ነጋቸውን ዛሬ ላይ ለመመሥረት በተስፋ መስከረም ላይ ይታነጻሉ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በአማራ ክልል በጸጥታ ችግር ምክንያት ሕጻናት የመስከረም ተስፋቸውን በትምህርት ገበታ ተገኝተው እንዳይቀርጹ እንቅፋት ተፈጥሮባቸዋል።
ጥቁሩ ሰሌዳ ጠመኔን ናፍቋል፤ ወንበሮች ተማሪዎችን ተመኝተዋል፤ በርካታ ሕጻናትም የትምህርት ቤቱ ግቢ ናፍቋቸዋል፤ የግቢው ሳሮች መልካም መዓዛ ሕጻናትን ይጣራሉ።
በአማራ ክልል በጸጥታ ችግር ምክንያት በ2018 ዓ.ም ከ3 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው ነበር። በርካታ ትምህርት ቤቶችም ተዘግተው መቆየታቸው ይታወሳል። በክልሉ በ2019 የትምህርት ዘመን 7 ነጥብ 6 ሚሊዮን ተማሪዎች በትምህርት ገበታ እንዲገኙ እየተሠራ ይገኛል።
ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው እንዲገኙ፤ ሰሌዳ ከጠመኔ ጋር እንዲጣመር፤ ወንበሮች ከሕጻናት እና ከደብተሮች ጋር እንዲጣመሩ፤ የትምህርት ቤቱ ግቢ በተማሪዎች ተስፋ እንዲሞላ፤ የሕጻናቱ ጨዋታ በግቢውን እንዲያደምቅ፤ በመስኩ ላይ የነገ ራዕያቸው እንዲበቅል ሰላምን ማጽናት ያስፈልጋል።
የሰላም እጦት የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ይገድላል፤ የሕጻናትን ራዕይ ይቀብራል፤ የመልካምነት እሴትን አጥፍቶ የመገዳደል ጎጅ ባሕልን በአዕምሯቸው ላይ ይተክላል።
ሰላምን ማጽናት፤ አፈ ሙዝን መዝጋት፤ ለሕጻናት ተስፋ እና ዕድገት የሰላምን ነጭ አርማ መያዝ ያስፈልጋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
