
የክረምቱ ዶፍ ዝናብ ያልፋል፤ ጭጋጉ እና ቆፈኑ ይገፈፋል፤ የብርሃን ጮራ ምድርን ያሞቃታል። በዚህ ጊዜ አረንጓዴው መስክ ላይ ወርቃማዋ አደይ ከምድር ማኅፀን ፈንድታ ምድርን ታስውባለች።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብዝኀ ሕይወት ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው የአደይ አበባ በሳይንሱ ‘ባይደንስ’ እንደምትባል ይገልጻሉ። ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ላይ ሚዲያ በሰጡት ትንታኔ መሠረት በኢትዮጵያ ከሚገኙት 20 ዝርያዎቹ ውስጥ ‘ማክሮፕተራ’፣ ‘ፕሬስቲናሪያ’ እና ‘ፓክሎማ’ በብዛት የሚበቅሉ ብርቅዬዎች ናቸው።
ከእነዚህም መካከል ‘ባይደንስ ማክሮፕተራ’ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ ልዩ ዝርያ ነው። አደይ ተራ አበባ አይደለችም፤ የተፈጥሮ የጊዜ ሰሌዳ ማሳያ እንጂ። የትዕግሥት፣ የተስፋ እና የብሩህ ዘመን መልዕክተኛም ናት።
አደይ የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት አብሳሪ ናት። ይህ የኾነው በጥልቅ ተምሳሌትነቷ ነው። በክረምት ብርድ እና ጭቃ ውስጥ ተደብቃ ትቆያለች።
ፀሐይ ስትወጣ እና ሰማዩ ሲጠራ ግን ብቅ ትላለች። ፕሮፌሰር ሰብስቤ ይህንን ዕውነታ በሳይንሳዊ ዕይታ ያስረዳሉ።
አደይ አበባ በመስከረም ወር አብቦ ዘሩን መሬት ውስጥ የሚያቆየው በተፈጥሯዊ ዑደቱ ነው። የመስከረም አየር ንብረት ለእሱ እጅግ ተስማሚ በመኾኑ ማበቢያው ከኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ጋር በአጋጣሚ ሊገጣጠም ችሏል ነው የሚሉት።
አደይ የዘመኑን መለወጥ ታበስራለች። በየሜዳው እና በየተራራው በኅብረት ትፈካለች። ደማቅ ቀለሟ የፀሐይ ብርሃንን ይመስላል።
አረንጓዴዋን ምድር በወርቅ ታስውባለች። የፈጣሪን የጥበብ አሻራ በገሃድ ታሳያለች። አደይ የጨለማ ማለፍ፣ የተሰለቸ ዓመት ማሳለፊያ፣ የአዲስ ሕይወት መጀመር ማብሰሪያም ናት።
አደይ የዘመን ድልድይ ናት። ዕድሜዋ እጅግ አጭር ቢሆንም በታላቅ ድምቀት ትፈካለች።
የሰውን ልጅ ልብ በሐሤት ትሞላለች። ክረምት አለፈ፣ በጋ መጣ ብላ ታውጃለች። ይህንንም ያለ ቃል በውበቷ ትሰብካለች። ልጃገረዶች “እንቁጣጣሽ” እያሉ ይዘምራሉ።
በዚህ ጊዜ አደይ በእጆቻቸው ላይ ትደምቃለች። የንጽሕና፣ የሰላም እና የፍቅር ምልክት ትኾናለች።
አሮጌው ዘመን በአዲሱ ይተካል። ምድር ጭቃዋን ታጥባ አረንጓዴ ትለብሳለች። ልክ እንደ አዲስ ሙሽራም ታጌጣለች። አደይ የዚች ሙሽራ የራስ ላይ ዘውድ ናት። የልምላሜዋም ደማቅ መግለጫ ነች።
አደይ ስትፈካ የሰው ልጅ ልብም አብሮ ይፈካል፤ ያረጀ ቂም ይረሳል። አዲስ የሕይወት ምዕራፍ ይጀመራል። ለዚህም ነው አደይ ከተራ ዕፅዋትነት ያለፈችው።
በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ የመታደስ ምልክት ኾናለች። የይቅርታ እና የብሩህ ተስፋ ቋንቋም ናት። የዘመናት አብሳሪነቷንም በክብር እና በውበት ተላብሳ ትኖራለች።
#አደይ #አዲስ_ዓመት #አሚኮ #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_02_2019_ዓ_ም
በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
