🌼አንድ ሀገር ብዙ ዓለም _ኢትዮጵያ 🇪🇹

9

 

በቅዱሳት መጻሕፍት ስሟ በክብር የተነሳላት፤ የታሪክ እልፍኝ እና የሰው ዘር መገኛ ድንቅ ምድር፤ ጠላቶች አበቃላት ብለው ቃል ሲያዉጁ ጸንታ የምትቆም ረቂቅ፤ ፈረሰች ሲባል ይበልጥ የገነነች፤ ተከፋፈለች ሲሏት አንድነቷን ያጠነከረች ምስጢራዊት፣ ከራሷ አልፎ ለሌሎች የተረፈ የነጻነት ችቦ ለኳሽ፤ ተፈጥሮ ሳይሰስት ውበቱን እና ፀጋውን የቸራት የውበት ሰገነት፤ ከድንቅ መልክዓ ምድራዊ ስብጥሯ እስከ ኅብረ ብሔራዊ የሕዝቧ አኗኗር አንድ ሀገር ብዙ ዓለም የተሰኘች ኢትዮጵያ።

ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያሉ ልጆቿ ጥበበኞች፤ የዓለምን ዐይን የማረኩ እንደ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የአክሱም ሐውልት፣ የጎንደር አብያተ መንግሥታት እና የሐረር ጀጎል ግንብ ያሉ የቱሪስት መስህቦችን ያነጹ ናቸው። እሷ የታሪካዊት እና የጥንታዊ ሥልጣኔ ሕያው ምስክርም ናት ይሏታል ደራሲ ከበደ ሚካኤል።

በአዲስ ዓመት፣ በመስቀል፣ በጥምቀት፣ በመውሊድ እና ዒድ፤ በኢሬቻ፣ ጫምባላላ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል እና በሌሎች በዓላት እና ባሕሎች በሚታየው ኅብረ-ቀለማት እና የሕዝብ አብሮነት ዓለም የሚደነቅባት ባለፀጋ ስለመኾኗም ያትታሉ።

ሜዳ ስናቋርጥ፤ ዳገት ስንወጣ፤ ቁልቁለት ስንወርድ፣ ወንዝ ስንሻገር፤ ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላኛው ከተማ ስንቀሳቀስ ዐይናችን የሚያየው አዲስ፣ ጆሯችን የሚሰማው ብርቅ እና ድንቅ የኾነባት እያደር አዲስ ምድር ናት።

በጉያዋ አቅፋ የያዘቻቸው ቋንቋዎች፣ ባሕሎች እና እሴቶች የልዩነት ምክንያቶች ሳይኾኑ የየማኅበረሰቡ መገለጫዎች ናቸው። የዚህ ማኅበረሰብ የጋራ ስም እና መጠሪያው ደግሞ “ኢትዮጵያዊ” ነው። ይህ ስም ደግሞ ምስጢር ነው።

ይሄ ሁሉ ዓለም የሚቀናበት ክብር እና እምቅ ሀብት ዛሬ ላይ ለአንዳንዶች “በእጅ የያዙት ወርቅ…” የኾነ ይመስላል። የራሳችንን ድንቅ ባሕል እና እሴት አሳድጎ እና ጠብቆ ለዓለም ከማስተዋወቅ እና ለትውልድ ከማስተላለፍ ይልቅ አጉል የፖለቲካ እና የብሔር ፉክክር ውስጥ ገብተው አባቶች በደም እና በአጥንት ያስረከቡትን ድንቅ እሴት ለማጠልሸት ደፋ ቀና ሲሉ ይስተዋላሉ።

እውነታው ግን ወዲህ ነው፣ ባሕል እና እሴቷ የደበዘዘ ቢመስል የማይጨልም፤ አንድነቷ የላላ ቢመስል እንደማይበጠስ፤ ታሪኳ የሚረሳ ቢመስልም ደምቆ የሚነበብ፤ ተፈጥሮዋ የሚቀያየር ቢመስልም ቋሚ፤ ሐቋ የሚካድ ቢመስልም ሕያው፤ ደሃ ብትመስል ባለፀጋ፤ ኋላ ቀር ብትመስል ሥልጡን፤ የሚያፈርሷት ብትመስልም ከትውልድ ትውልድ የምትሻገር መኾኗን ሚስጢረኞቿ ጠንቅቀው ያውቁላታል።

ታዋቂው ሴኔጋላዊ የታሪክና አንትሮፖሎጂ ተመራማሪ ሼክ አንታ ዲዮፕ እንደሚሉት ማንም እግሩ ንቃቃት እስከሚያወጣ ዓለምን ቢጓዝ እንደ ኢትዮጵያ ያለ የምድር ገነት አያገኝም ብለው መስክረውላታል።

እናም ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ፣ ትውልድ አልፎ ሌላ ትውልድ ሲመጣ ተጠብቆ የቆየው ይህ ድንቅ እሴት እና አንድነት አሁንም በትጋት ተጠብቆ፣ አድጎ እና ጎምርቶ ለቀጣዩ ትውልድ እንደሚተላለፍ ይናገሩላታል፥ ብዕራቸው ሳይቆራረጥ በደማቁ ይጽፉላታል።

እኛም በአዲሱ ዓመት ለአንድ ዓላማ ቃል እንግባ፣ ከአጉል ፉክክር ወጥተን፤ አንዳችን የሌላውን ማንነት አክብረን፤ የተለያዩ ማንነቶቻችንን የውበታችን መገለጫ አድርገን፤ ይህችን አንድ ሀገር ብዙ ዓለም የኾነች ኢትዮጵያችንን በጋራ እንጠብቅ።

መልካም አዲስ ዓመት 🙏

#አሚኮ #አዲስ_ዓመት #አንድ_ሀገር_ብዙ_ዓለም #ኢትዮጵያ 🇪🇹

#ድንቅ_ምድር_ኢትዮጵያ #አዲስ_ዓመት #አሚኮ #ኢትዮጵያ🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_02_2019_ዓ_ም

በአድኖ ማርቆስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article‎አደይ – የዘመን ትንሣኤ እና የተፈጥሮ የቃል ኪዳን ማኅተም
Next article“የብሪክስ መድረክ የጋራ ትብብርን ወደ የጋራ እሴት፣ ጽናት እና ዘላቂ ዕድገት የመለወጥ ሰፊ አቅምና ቁርጠኝነት አለው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር)