‎ መስከረም – የተፈጥሮ መታደስ ወር

6


‎”መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ
‎እንኳን ሰው ዘመዱን ይጠቃል ባዕዳ… የሚለው ስንኝ፣ የዘመናት የኢትዮጵያዊነት መገለጫ የኾነውን ማኅበራዊ ትስስር የሚያሳይ እውነታ ነው። አዲስ ዓመት ሲተካ ከተፈጥሮ መታደስ ባሻገር የሰዎች ግንኙነት የሚታደስበት፣ የሩቅ ዘመዶች የሚቀራረቡበት እና የትውስታ ድልድዮች የሚገነቡበት ልዩ ወቅት ነው መሥከረም።

‎​ይህ ወር የክረምቱን ደመና አራግፎ የፀሐይን ብርሃን ይዞ ሲመጣ፣ የሰዎች ልብም አብሮ ይሞቃል። የበዓል አቀባበል ከቁሳቁስ ዝግጅት ባለፈ ከወዳጅ ዘመድ እና ከጎረቤት ጋር ያለውን ቁርኝት ማጠናከሪያ አጋጣሚ ነው። በከተማ እና በገጠር ያለው ኅብረተሰብ አሮጌውን ዓመት በሰላም ላሻገረው ፈጣሪ ምስጋና እያቀረበ አዲሱን ዘመን በደስታ ይቀበላል፤ ይጠያየቃል።

‎​በዚህ ወቅት የሚደረግ መጠያየቅ የ”አብሮነት እሴትን በግልጽ ያሳያል። መሥከረም የቀን መቁጠሪያ መለወጫ ብቻ ሳይኾን የሰብአዊነት መታደሻ ነው። ከዘመድ ጋር መገናኘት እና የጤና ባለቤት መኾናቸውን ማረጋገጥ ለኑሮ ትርጉም ከሚሰጡ እጅግ ውብ ባሕላችን መካከል ይመደባል።

‎እንቁጣጣሽ ሲመጣ መጠያየቅ እና መልካም ምኞትን መለዋወጥ ግንባር ቀደም እሴቶች ናቸው። ይህን የመጠያየቅ ባሕል በፊት በእግር ጉዞ የሩቅ ዘመድ ይጠያየቃል። አኹን ላይ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጓደኛ እና የሥራ ባልደረቦች እርስ በእርስ በመገናኘት፣ በስልክ በመደወል ወይም በአጭር የጽሑፍ መልዕክቶች “እንኳን አደረሰዎት”በማለት ሰላምታ ይለዋወጣሉ።

‎በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ሥብከት የማኅበራት ማደራጃ ክፍል ኀላፊ ርእሰ ርኡሳን ቆሞስ አባ ኅይለማርያም ታገለ መስከረም የተፈጥሮ መታደስ ብቻ ሳይኾን፣ የሰው ልጅም ነፃነትን የሚጎናጸፍበት ወቅት ነው ይላሉ። የደከመው የሚበረታበት፣ ሰዎች በነፃነት የሚንቀሳቀሱበት እና ሰማይ እና ምድር የሚተያዩበት ወር ነው ይላሉ።

‎ጨለማው ሲገለጥ በርካታ በረከቶች ይዞ ተስፋን ያጭራል። የክረምት ዝናብ የነበረው ሀገራችን ደመናው ይገፈፋል፣ ወንዞች ይጎድላሉ፣ ፀሐይም ትወጣለች። ሜዳዎች በፀሐይ ሙቀት ሲገለጡ ሰውም እንደፈለገ የሚንቀሳቀስበት በመኾኑ “መስከረም ሲጠባ ባዳም ይጠየቃል” ይባላል።

‎​ክረምት ለመንቀሳቀስ ይቸገር የነበረው ሕዝብ በዚህ ወር ነፃነትን አግኝቶ ይገናኛል፣ ይተያያል እንዲሁም ይጠያየቃል። ይህ ወቅት መልካም በመኾኑ በበጎ የምንዘጋጅበት ነው ብለዋል። ያልተያዩ የሚተያዩበት፣ የተራራቁ የሚቀራረቡበት፣ “ጨለማው አለፈ፣ ዝናቡ ተመለሰ” ተብሎ በደስታ የሚታሰብበት ነው።
‎​
‎መስከረም ወር የብርሃን መውጫ እና የድል ምዕራፍ ነው። በዚህ ወቅት የደመናው መበተን ሕዝቡ እንደ ልብ ተንቀሳቅሶ የዕለት ስንቁን እንዲሰንቅ ያስችለዋል። ጨለማው አለፈ፣ ብርሃኑ መጣ” እየተባለ በደጅ የሚበራ ችቦ ተይዞ የሚከበርበት የኢትዮጵያዊነት መገለጫ መኾኑንም ነው የገለጹት። ሕጻናት የሚበራ ችቦ ይዘው በየደጁ እየዞሩ ሰው ሳይመርጡ “እመዬ፣ ባብዬ” በማለት እንቁጣጣሽ እያሉ ይጠይቃሉ ብለዋል።
‎መሥከረም የፍቅር ወር መኾኑን ሲያስረዱ።

‎እንቁጣጣሽ ከክረምት ትግል በኋላ የሚገኝ የፍሬ፣ የሰላም እና የአዲስ ተስፋ ምዕራፍ ነው። አዲሱን ዓመት ስንቀበል ባለፈው ዓመት የነበሩትን አለመግባባቶች አስወግደን፣ በአዲስ አስተሳሰብ እና በይቅር ባይነት መንፈስ ለሀገራችን መልካም ሥራዎችን የምናበረክትበት ዘመን እንዲኾንም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

‎ይህ የባሕል ሥርዓት የኅብረተሰቡን መተሳሰብ እና መከባበር ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚያሻግር ትልቅ ማኅበራዊ ኀይል ነው።

‎#አሚኮ #አዲስ_ዓመት #መሥከረም_ወር #ኢትዮጵያዊ🇪🇹

‎#ባሕር_ዳር #መስከረም_02_2019_ዓ_ም

‎በሥራውድንቅ ደሳለው

‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር በመኾኗ ምን ተጠቀመች ?