
ኢትዮጵያ በታሪኳ ረጅም እና ጠንካራ የዲፕሎማሲ መሠረት ያላት፣ ለአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ምስረታ ግንባር ቀደም ሚና የተጫወተች የነጻነት እና የዲፕሎማሲ ማዕከል ናት።
አሁንም ሀገሪቱ ብሔራዊ ጥቅሟን፣ የሕዝቧን የብልጽግና ጉዞ እና ቀጣይነት ያለው እድገቷን ለማረጋገጥ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ ካሉ የዓለም ሀገራት ብሎም የቡድን ጥምረቶች ጋር አጋርነቷን እያጠናከረች ትገኛለች። በዚሁ መሠረት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) የተመራ ታሪካዊና ስትራቴጂካዊ የዲፕሎማሲ ጥረት፣ ኢትዮጵያ ከጥር 2016ዓ.ም ጀምሮ የብሪክስ (BRICS) አባል ሀገር እንድትኾን አስችሏል።
ብሪክስ (BRICS) በ2001ዓ.ም በብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ እና ቻይና የተመሠረተ ነው። በ2003ዓ.ም ደቡብ አፍሪካን በይፋ በማካተት ጥምረቱን አጠናክሯል። ትብብሩ በሦሥት ዋና ዋና አምዶች ላይ የተመሠረተ ነው። ይህም ፖለቲካ እና ጸጥታ፣ ኢኮኖሚ እና ፋይናንስ፣ የሕዝብ ለሕዝብ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ናቸው። የጥምረቱን ዓላማ ለማሳካትና ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ፣ በበርካታ ሀገራት ዘንድ የመቀላቀል ጥያቄዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስት ሀገራት በ2016ዓ.ም ብሪክስን በይፋ ተቀላቅለዋል።
አሁን ላይ የጋራ ዕይታ ያላቸው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ የኾኑ፣ ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ የሚገኙ 11 ሀገራትን አቅፏል። በአጋር ሀገርነት ደረጃም ከበርካታ ሀገራት ጋር በተለያዩ የትኩረት መስኮች ላይ በትብብር በመስራት ላይ ይገኛል። ስብስቡ የዓለማችንን ከ45 በመቶ በላይ የሕዝብ ብዛት የያዘ ነው። በመግዛት አቅምም የዓለምን 35 በመቶ የሚኾነውን ጠቅላላ የውስጥ ምርት (GDP) ይሸፍናል።
ብሪክስ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መተዳደሪያ ደንቦችን የሚያከብር እና የባለብዙ ወገን ትብብርን በሚያከብር መርህ የሚመራ ነው። አሁናዊ የዓለም አቀፉን መዋቅር ይበልጥ የሚያጠናክር፣ ፍትሐዊ፣ አሳታፊ እና አካታች ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ አቋም ያለው ስብስብ ነው፡፡
ይህ ታላቅ እና በማደግ ላይ የሚገኝ ስብስብ በየዓመቱ ከአባል ሀገራቱ በሚመረጥ መራሔ መንግሥት ሰብሳቢነት የሚዘጋጅ ነው። ሀገራቱ በውይይታቸው በጋራ በሚስማሙባቸው እና በሙሉ ድምጽ በሚያጸድቁት ላይ የጋራ አቋም ይይዛሉ፤ በትብብር አብሮ የመሥራት ስምምነቶችን ያደረጋሉ። በተያያዘ 18ተኛው የብሪክስ ስብሰባ በሕንድ አዘጋጅነት በወርኃ መስከረም 2019ዓ.ም እየተከናወነ ይገኛል።
✍️ብሪክስን የመቀላቀል ጉዞ
ኢትዮጵያ የብሪክስ ቡድንን ለመቀላቀል ፍላጎቷን በመግለጽ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) ቀጥተኛ እና ታሪካዊ የዲፕሎማሲ መሪነት በነሐሴ 2015ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ በነበረው 15ተኛ የብሪክስ ጉባዔ ላይ ጥያቄዋ ተቀባይነትን አግኝቶ፣ በጥር 2016 ዓ.ም በይፋ መቀላቀሏ ይታወሳል፡፡ አሁን ላይ ከ11 የብሪክስ አባል ሀገራት ውስጥ አንዷ ኾና በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ የራሷን ጉልህ ሚና እየተጫወተች ትገኛለች፡፡
✍️ የእስካሁን እና የቀጣይ ፋይዳው
ኢትዮጵያ በሕዝብ ቁጥርም ኾነ በኢኮኖሚ በማደግ ላይ በምትገኝበት በዚህ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ብሪክስን መቀላቀሏ ከስብስቡ እና ተያይዘው የሚመጡ የኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝም፣ የቴክኖሎጂ፣ ገበያ እና መሰል በርካታ ዕድሎች ተጠቃሚ እንድትኾን አድርጓታል፡፡
ወሳኝ የኾኑ ዓለም አቀፍ አጀንዳዎች ላይ የሚመክር፣ የጋራ አቋም በሚይዘው የዚህ ስብስብ አካል በመኾኗ ኢትዮጵያ ድምጿን እንድታሰማ፣ ሀገራዊ ጥቅሟን እንድታስጠብቅ እና አህጉራዊ ድምጽ እንድትኾን ያስችላታል፡፡ ለአብነት በ17ተኛው ጉባዔው ላይ ስብስቡ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን የንግድ ተቋም ለመቀላቀል የምታደርገውን ጥረት በሙሉ ድምጽ እንደሚደግፍ የአቋም መግለጫ ይዟል።
በተያያዘም የብሪክስ አባል በመኾኗ አሁን ላይ ተሰሚነቷ ከማደጉም በላይ በፋይናንስ፣ ኢንቨስትመንት እና መሰል የዕድገት መሰረተ ልማት ትብብሮች ላይ አማራጮችን አበርክቶላታል።
ለዚህም ኢትዮጵያ የኒው ዴቨሎፕመንት ባንክን በአባልነት መቀላቀሏ ለሀገራዊ የልማት ፋይናንስ፣ ለመሠረተ ልማት ደጋፍ እና ለማክሮ-ኢኮኖሚ መረጋጋት አማራጭ የገንዘብ ምንጮችን ለማግኘት የሚያስችላት፣ ከደቡብ ደቡብ የፋይናንስ ሥርዓቶች ጋር የሚኖራትን ትስስር የሚያጠናክር በመኾኑ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ57ተኛ መደበኛ ስብሰባው ለኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ ማቋቋሚያ ስምምነት የአባልነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅን አጽድቋል፤ በአሁኑ ወቅትም ሂደቱ በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያውያን ወጣቶችም በተለያዩ የብሪክስ የወጣቶች ማዕቀፍ ውስጥ በሥራ ፈጠራ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ ሳይንስ እና መሰል መስኮች ላይ በንቃት እየተሳተፉ ይገኛሉ። እየተፈጠሩ በሚገኙ የኢንቨስትመንት እድሎችም በርካታ የሥራ እድሎች እየተፈጠረላቸው ይገኛል። ከአባል እና አጋር ሀገራቱ ወጣቶች ጋር ትስስር የመፍጠርና ልምድ ልውውጥ የማድረግ ዕድሎችን አስገኝቶላቸዋል፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሐፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ኢትዮጵያ ስልታዊ፣ በመርሕ የሚመራ እና ሀገራዊ ጥቅምን ያስቀደመ የዲፕሎማሲ መሪነት እያከናወነች ባለችበት በዚህ የታሪክ ምዕራፍ የመንግሥት ተቋማት፣ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ ወጣቶች፣ ታዳጊዎች እና መላው ኢትዮጵያውያን ሀገሪቱ በእጇ ያለውን ዕድል በመረዳት እና በጨመረ ንቃት ራስን ዝግጁ በማድረግ ለሀገር እድገት በጋራ መሥራት እንደሚገባ ተመላክቷል።
#ኢትዮጵያ_ስኬታማ_ዲፕሎማሲ #ብሪክስ
#ባሕር_ዳር #መስከረም_02_2019_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
