
የሰላም ይሁንልን የሰላም ይሁንልን፤ አዲሱ ዓመት አዲሱ ዘመን። በማለት በመልካም ሞኞት ዓመቱን ይጀምራሉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች።
የክረምቱ ዝናብ ኀያል ኾኖ፤ ወንዞች ሞልተው፤ ዘመድ አዝማድ መገናኘት አቁሞ ለወራት በመራራቁ ምክንያት ማኅበረሰቡ ክረምት አልፎ አዲስ ዓመት ሲመጣ “የጨለማው ዘመን አለፈ ብርሃን ተተካ” ይላል።
አዲስ ዓመትን እንደ ክዋክብት በፈካ፤ እንደ ወርቅ በጠራ ተስፋ ይቀበሉታል። ነጋቸውን ብሩህ ለማድረግ ዛሬያቸውን በኅብረት፤ በአንድነት፤ ማዕድ በመጋራት በፍቅር እና በሰላም ያሳልፉታል።
የሩቅም የቅርብም ዘመድ ተገናኝቶ ዓመቱ የሰላም እንዲኾን በምርቃት ያሳርጉታል። የተነፋፈቁ ይገናኙበታል፤ የተጣሉ ይታረቃሉ፤ የተቸገሩ ይካፈሉበታል፤ ስለ አብሮነታቸው ያወሩበታል፤ የዓመት ዕቅዳቸውን ይጋሩበታል፤ ሰለ ሀገር ሰላም ይማልዱበታል። በአዲሱ ዓመት አዲስ ነገርን ይጠብቁበታል።
በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ግን የበዓል ድባብ በመጠኑም ቢኾን ቀንሷል። የተነፋፈቁ ለመገናኘት የጸጥታ ችግር እንቅፋት ኾኖባቸዋል። እናት በዓውደ ዓመት ልጆቿን ለማየት ተቸግራ ቆይታለች። ተሠባሥቦ በዓልን ለማሳለፍ የናፈቁ በጸጥታ ችግር መሄድ አቅቷቸው ቆይተዋል። ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች ደግሞ በኅብረት ተሠባሥበው ያሳልፋሉ።
በአዲሱ ዓመት ስለ ሰላም ይማልዳሉ፤ ሰላምን ይሰብካሉ። ማኅበረሰቡ ሰላምን ናፍቋል፤ የሰላም አማራጭ የሚቀበሉ ታጣቂዎችን በፍቅር ተቀብሏል።
እናቶች ወደ ተሻለ ሆስፒታል ተጉዘው የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ፤ ሕጻናት ወደ ትምህርት ገበታ እንዲያቀኑ፤ ገበሬ ምርቱን እንዲሠበሥብ፤ ነጋዴ ተንቀሳቅሶ እንዲነግድ ሰላምን ማጽናት ያስፈልጋል።
በአዲሱ ዓመት ወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው፤ በሥራቸው ውጤታማ እንዲኾኑ፤ ከቦታ ቦታ በነጻነት ተንቀሳቅሰው እንዲሠሩ፤ ነጋቸውን ዛሬ ላይ ዕውን እንዲያደርጉ ሰላምን ማበርከት ጥያቄ ውስጥ የማይገባ ጉዳይ ነው።
ሕጻናት የጤና ክትባቶችን እንዲያገኙ፤ የኢኮኖሚ መነቃቃት እንዲፈጠር፤ የኑሮ ውድነት እንዲረጋጋ፤ የሀገር ዕድገት እንዲሳለጥ የአፈሙዝ ላንቃን በመዝጋት የሰላምን ማዕድ መካፈል ይገባል።
የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እንድሪስ ከሰሞኑ ከሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ የሰላምን ዋጋ የምንረዳው እንደ ጤና ስናጣው ነው ብለዋል።
ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲሄዱ፤ ገበሬው ምርቱን እንዲሠበሥብ፤ ነጋዴዎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው እንዲነግዱ፤ ዜጎች በየቦታው በነጻነት ተንቀሳቅሰው እንዲሠሩ ሁሉም የበኩሉን ሚና በመወጣት ሰላምን በአዲሱ ዓመት እንዲያጸና አሳስበዋል።
ሰላምን ማጽናት፤ ጥላቻን ማስወገድ፤ ጥላቻ የሚዘሩ አካላትን በቃችሁ ማለት፤ በደል እና ቁርሾን ከማንሳት ይልቅ ይቅር ባይነትን ማስቀደም በአዲሱ ዓመት ከሕዝቡ የሚጠበቅ ተግባር መኾኑን አሳስበዋል።
#አሚኮ #ሰላም #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_02_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
