
የኢትዮጵያ ሰማይ በጠላት ኃይል እንዳይጣስ፣ ምድሯ በሰማይ ተምዘግዛጊ ጀቶች፣ በዘመናዊ ድሮኖች፣ በጦር አውሮፕላኖች እንዲጠበቅ አድርጓል።
የመከላከያ ሠራዊት ከሠራዊቱ መዘመን ባሻገር ለቴክኖሎጂ እና ለአየር ኀይሉ በሰጠው ትኩረት የኢትዮጵያን ሰማይ አይደፈሬ እንዲኾን አስችሏል።
የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ በክብር ተጠብቆ ከትውልድ ትውልድ እንዲሸጋገር፣ ጠላቶቿ ትንኮሳን ሲመኙ ደጋግመው እንዲያስቡ፣ ከኢትዮጵያ አልፎ የቀጣናው ሰላም የተረጋገጠ እንዲኾን የአየር ኀይሉ ከፍተኛ ሚናን ተወጥቷል።
በተምዘግዛጊ ጀቶቹ፣ ከዐይን ጥቅሻ በሚፈጥኑ ድሮኖቹ፣ እንደ ንሥር ኢላማን ነጥሎ ማየት በሚችሉ የጦር አውሮፕላኖቹ ሥር ሠንደቋን አስፍሮ ዘወትር ከፍ ብላ እንድትታይ አድርጓል።
ለመከላከያ ሠራዊት እና ለአየር ኀይሉ ሠንደቅ ዓላማ አንድ ቀን ብቻ የሚከበር አይደለም፤ ይልቁንስ በየዕለቱ በየተራራ እና ሸንተረሩ፣ በየሀሩሩ እና በውርጩ ስለ ክብሯ ይዋደቁላታል እንጅ።
በክንዳቸው እና በደረታቸው ሠንደቋን አሥቀምጠው፣ በልባቸው ደግሞ ፍቅሯን እና ክብሯን አትመው ለዘመናት በጽናት ቁመዋል። ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሠው፣ የማይተካ ሕይወታቸውን መስዋዕት አድርገው ለሠንደቅ ዓላማ ያላቸውን ታማኝነት ለዘመናት በጽናት አስመስክረዋል።
ከንሥር በሚልቅ ፍጥነቱ ለጠላቶች ምትሐት ኾኗል፣ በጥልቅ ምልከታው የጠላትን ዒላማ ነጥሎ ይመታል፣ ከዐይን ጥቅሻ የሚፈጥነው ጥቃቱ ጠላቶች ክብሯን ለመዳፈር እንዳያስቡ አድርጓቸዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኀይል ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት እና ክብር ለዘመናት በጽናት ጠብቋል። በዚህም ጠላቶች የኢትዮጵያን ሰማይ ለመጣስ ቀርቶ ለማየት እንዳይደፍሩ አድርጓል።
ተቋሙ ዘመናዊ የአየር ክትትል፣ የራዳር ሥርዓቶች፣ የአየር መከላከያ አቅሞችን እና የአውሮፕላን ጥገና አቅሙን አሳድጓል። አየር ኀይሉ በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኀይል ሥልጠና እና የዝግጁነት አቅምን በማሳደግ የሀገሪቱን የአየር ክልል አይደፈሬ አድርጓል።
ከትናንት እስከ ዛሬ በሰመረ የጸና አቋሙ፣ በከፍተኛ የውጊያ ብቃቱ እና በታሪካዊ የጀግንነት ገድሎቹ የሀገሪቱን ዳር ድንበር ከውጭ ጠላቶች እና ስጋቶች በጽናት በመከላከል ታሪካዊ ክብሩን አስቀጥሏል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ 19ኛውን ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን አሥመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት የመከላከያ ሠራዊት እና የጸጥታ አካላት የሀገር አለኝታ፣ የሕዝብ ደኅንነት ዋስትና እና የሉዓላዊነታችን ታማኝ ጠባቂዎቻችን ናችሁ ብለዋል።
ለተከበረው ሠንደቅ ዓላማ በበርሃ፣ በዱር፣ በውርጭ እና በሀሩር ሀገርን ከውስጥ እና ከውጭ አደጋ ለመጠበቅ የምትከፍሉት መስዋዕትነት በትውልድ ሁሉ ከበሬታ እና ሞገስን ያገኛል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ አየር ኀይል አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በአንድ ወቅት ባደረጉት ንግግር አየር ኀይሉ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በሀገሪቱ ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን በመቀልበስ በኩል ከፍተኛ ጥረት አድርጓል ብለዋል። ከኢትዮጵያ አልፎ በታሪክ የአፍሪካ ሀገራትን ሉዓላዊነት እንዲከበር ማድረጉንም አንስተዋል።
አየር ኀይሉ በታሪኩ ወረራን በመቀልበስ፣ የአሸባሪ ታጣቂዎችን እንቅስቃሴ በማጥፋት ከፍተኛ ድል መጎናጸፉን ገልጸዋል። ለኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት፣ ሰላም እና ነጻነት መስዋዕትነት የከፈለ ብርቅየ ተቋም መኾኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኀይል ምክትል አዛዥ ለከባድ ጥገና ማዕከል ብርጋዴል ጄኔራል መሠረት ጌታቸው በተቋሙ ቴክኖሎጂን የማምረት፣ የመጠገን እና የመፈጸም አቅም ማደጉን ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ የሚተርፍ አቅም መፍጠር ተችሏልም ነው ያሉት። ለብሔራዊ ጥቅም የሚመጥን አቅም ለመገንባት በቁርጠኝነት እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። በዚህም የኢትዮጵያ ጠላቶች ኢትዮጵያን ከመተንኮሳቸው በፊት ደጋግመው እንዲያስቡ አስገድዷቸዋልም ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
