‎ሰንደቅ ዓላማ የክብር ማኅተም የነጻነት አውራ

10
🇪🇹
‎ሰንደቅ ዓላማ ከቀለም እና ከጨርቅ ጥንቅር እጅግ የላቀ የዘመናት ታሪክ፣ የሕዝብ ማንነት እና የሀገር ሕልውና ሕያው ማኅተም ነው። ‎ሀገር በሕይወት መኖሯን፣ ሉዓላዊነቷን እና ክብሯን በዓለም አደባባይ የምታውጅበት የመጨረሻው የነጻነት ቋንቋ በመኾኑ ሀገር እና ሰንደቅ ዓላማ የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው።
በዚህም ምክንያት ሰንደቅ ሲደፈር ሀገር ትዋረዳለች፤ ሰንደቅ ሲከበር ደግሞ የሀገር ልዕልና ከፍ ይላል። ‎አንድ ዜጋ ሰንደቅ ዓላማውን ቀና ብሎ
ሲመለከት የሚያየው ከፍ ብሎ የሚውለበለበውን ጨርቅ ብቻ አይደለም፤ ያንን ክብር ለማምጣት የተከፈለውን የጀግኖች ደም፣ የደቀቀውን አጥንት እና የፈሰሰውን ዕንባ ጭምር እንጂ። ‎በኢትዮጵያም የዚህ ብሔራዊ ዓርማ ትርጉም ይበልጥ ጥልቅ፣ ስሜት ቀስቃሽ እና ቅዱስ ቁርኝት
ያለው ኾኖ እናገኘዋለን። ‎ለኢትዮጵያውያን ሰንደቅ ዓላማ የፖለቲካ ሥርዓቶች መለዋወጫ ሳይኾን ትውልድ ከትውልድ ጋር የተጋመደበት የማይበጠስ የቃል ኪዳን ገመድ ነው። ‎የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የዓድዋን ተራሮች ተሻግሮ የዓለምን የታሪክ ምዕራፍ የቀየረ፣ ብሎም የጥቁር
ሕዝብን የነጻነት ትግል ያቀጣጠለ የፓን-አፍሪካኒዝም የትግል አርማ ነው። ‎አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማቱ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው በመውጣት የዓለም ጭቁን ሕዝብ የነጻነት፣ የተስፋ እና የክብር መለያ ለመኾን መብቃታቸው በዓለም ታሪክ ውስጥ ወደር የማይገኝለት የነጻነት
ተምሳሌት ያደርገዋል። ይህ ታላቁ ብሔራዊ ዓርማ የትላንቱን አኩሪ ታሪክ ብቻ ሳይኾን የዛሬውን የሀገር ግንባታ እና የነገውን የከፍታ ራዕይ በጉያው ያቀፈ ነው። ‎የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በሕዳሴው ግድብ ማማ ላይ ሲውለበለብም ኾነ በጂኦ-ፖለቲካዊ ትኩረት ውስጥ ሲነሳ “ኢትዮጵያ
በምንም ዓይነት የውጭ ጫና ፈጽሞ አትንበረከክም” የሚል የጸና አቋምን ለዓለም ያስተጋባል። ‎በእርግጥም ኢትዮጵያ እና ሰንደቅ ዓላማዋ የደም እና የነፍስ ትስስር አላቸው፤ ይሁን እንጂ ይህንን ክቡር ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጎ ማውለብለብ የሚቻለው በባዶ ዲስኩር አይደለም። ይልቁንም
የውስጥ አንድነትን በማጽናት፣ ሉዓላዊነትን በማስከበር እና ጠንካራ ሀገራዊ የኢኮኖሚ አቅም በመገንባት ብቻ የሚረጋገጥ ነው። ጠቅላይ
ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አጽንኦት ሰጥተው ሲናገሩ ሰንደቅ ዓላማ የብሔራዊ መግባባት፣ የሉዓላዊነት እና በልዩነት ውስጥ ያለ አንድነት
ሕያው ማሳያ ነው። በመኾኑም የክብራችን እና የህልውናችን ምሰሶ የኾነው ሰንደቅ ዓላማችን ለዘላለም ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ፤ እያንዳንዱ ዜጋ
የሀገሩን ዕጣ ፈንታ በተመልካችነት ሳይኾን ሙሉ በሙሉ በባለቤትነት ስሜት ሊመራ ይገባል።
‎
‎
✍️ዘጋቢ:-ስማቸው አጥናፍ
‎
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleወርቅን ከስደት የመመለስ ጉዞ።
Next articleበመተማ ወረዳ በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀበሉ።