ወርቅን ከስደት የመመለስ ጉዞ።

2
ኢትዮጵያ ማህፀነ ለምለም ናት፤ ምድሯ ሁሉን አብቅሎ የሚመግብ ድንቅ አፈር ያዘለ፤ አፈሯ ወርቅ እና በርካታ ውድ የተፈጥሮ ገጸ በረከቶችን ያቀፈ ምድር።
ለኢኮኖሚ ዕድገቷ አይነተኛ ሚና መወጣት የሚችል እምቅ የወርቅ ማዕድን በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች እንዳላት በጥናት የተረጋገጠ ጉዳይ ነው።
ኾኖም ለዘመናት ይህ ከፍተኛ የወርቅ ክምችት ስለመኖሩ ሳይታወቅ በመቆየቱ፣ መኖሩ ከተረጋገጠ በኋላም ለዓመታት በአግባቡ መጠቀም ባለመቻሉ ለከፍተኛ ብክነት ሲዳረግ ቆይቷል።
አፈሯ ለዘመናት በጎርፍ ሲሸረሸር የማዕድን ሀብቱም አብሮ ተቧጥጦ ከሀገር ሲወጣ መኖሩ ይቆጫል። በዚህ ሂደት ምን ያህል ወርቅ አጥታ ሊኾን እንደሚችል በጥናት የተረጋገጠ ግልጽ ቁጥራዊ መረጃ ባይኖርም እጅግ ከፍተኛ ሊኾን እንደሚችል ይገመታል።
ኢትዮጵያ ወርቅ የማምረት እና የመላክ ሥራ ከጀመረች ከአንድ መቶ ዓመታት በላይ ቢኾናትም ሂደቱ ኋላቀር በኾኑ ዘዴዎች የሚከናወን በመኾኑ ውጤታማ እንዳልነበር ይነገራል።
የወርቅ ማውጫ ዘመናዊ ቴክኖሎጅ እና ማጣሪያ ፋብሪካ ባለመኖሩ በቁፋሮ እና ማጣራት ሂደት በከፍተኛ ሁኔታ በየወንዙ ሲባክን ኖሯል። በዚህ የቴክኖሎጅ እጥረት፣ በጎርፍ እና በኮንትሮባንድ የባከነው እልፍ ምርት ሀገርን ከድህነት የማውጣት ትልቅ ዕድል ነበረው።
አሁን ላይ ወርቅ የኢትዮጵያ ቁጭት ኾኗል። ይህንን የማዕድን ዘርፍ ከኋላ ቀር አሠራር የሚያስወጣ እና በማዕድን ዘርፉ የሚታየውን ከፍተኛ የቴክኖሎጂ እጥረት በዘላቂነት ለመቅረፍ መንግሥት ስልታዊ እርምጃዎችን መውሰድ ጀምሯል።
በቅርቡም ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ዘመናዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ አስመርቃለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካው ሥራ መጀመሩን ባበሰሩበት ወቅት እንደተናገሩት ሀገሪቱ ላለፉት አንድ መቶ ዓመታት በላይ ወርቅ ወደ ውጭ ብትልክም ከሚመረተው ወርቅ 60 እና 70 በመቶው ብቻ እየተወሰደ ቀሪው ቆሻሻ ተብሎ ይደፋ እንደነበር አስታውሰዋል።
የተገነባው ፋብሪካ ስለሚኖረው የላቀ የኢኮኖሚ ትርጓሜ ሲያብራሩም “የኢትዮጵያ ወርቅ ወርቅ መኾኑ ተረጋግጦ በብሔራዊ ባንኳ ውስጥ ቢቀመጥ እንኳን እንደ ገንዘብ አይቆጠርም ነበር። እንደ ገንዘብ የሚታየው ወደውጭ ተልኮ በማጣሪያ ፋብሪካ አልፎ ንጹሕነቱ ሲረጋገጥ ብቻ ነበር” ብለዋል።
ቀደም ሲል ያልተጣራው ወርቅ ወደ ውጪ ተልኮ ወደ ዶላር ከተመነዘረ በኋላ ወረቀቱ እንጂ ወርቁ ራሱ የሀገር ሃብት የማይኾንበት አሠራር እንደነበር አስታውሰዋል። የተገነባው የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ ይህንን አሠራር ሙሉ በሙሉ እንደሚቀይረውም ነው ያብራሩት።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመቶ ዓመታት ይህንን አቅም ባለመገንባቱ ብዙ ማጣቱን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ወሳኝ በኾኑ ዘርፎች ኢትዮጵያ ሠልጥና የአፍሪካ አርዓያ ኾና የማየት ሕልምን የሚያረጋግጡ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።
✍️ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“የሳይበር ደኅንነት የሀገር ደኅንነት ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next article‎ሰንደቅ ዓላማ የክብር ማኅተም የነጻነት አውራ