🌻”ከቤተሰብ ማዕድ ይልቅ የሕዝብ ሰላም ይበልጣል” የሰላም ዘበኞቹ የበዓል መስዕዋትነት

14

 

በዓል በመጣ ቁጥር ከዋዜማው ጀምሮ እስኪጠናቀቅ ከተሞች ደስ በሚል የገበያ ግርግር፣ በቄጠማ መዓዛ እና በጋራ ማዕድ ደስታ ይደምቃሉ።

ቤቶች በዘመድ አዝማድ ትስስር ሞቅ ብለው፣ አዲሱን ዓመት በደስታ ሲቀበሉ፣ በየመንገዱ ግን የሕዝብን ሰላም ለመጠበቅ በብርድ እና በፀሐይ የሚቆሙ የደንብ ልብስ የለበሱ የሰላም ዘበኞች አሉ።

ለብዙዎቻችን በዓል ማለት እረፍት፣ መዝናናት ፣ መብላት፣ መጠጣት እና ከወዳጅ ዘመድ ጋር መሠብሠብ ሲኾን ለእነሱ ግን የበዓል ቀን ማለት የከበደ የሕዝብ ኃላፊነት እና የላቀ መስዋዕትነት ነው።

ምክትል ኢንስፔክተር መላኩ ገብሬ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት የወንጀል መከላከል ክፍል ኀላፊ ናቸው። በሰላም ማስከበር ተግባር ላይ ከ20 ዓመታት በላይ ያገለገሉ የሀገር ባለውለታ ናቸው።

ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት አዲስ ዓመትን የተቀበሉት በቤታቸው ሳይኾን በሰላም ማስከበር ሥምሪት ላይ ነው።

በበዓላት ወቅት እንደማንኛውም ማኅበረሰብ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ግልገል አርደው፣ ማዕድ ቆርሰው በጋራ ውለው አያውቁም።
ባለቤታቸው እና ልጆቻቸው በዓል በመጣ ቁጥር፣ “ዘንድሮስ በዓልን አብረኸን አትውልም?” ብለው የሚጠይቋቸው ጥያቄ ሁልጊዜም ልባቸውን ይነካዋል።

“እንደማንኛውም ማኅበረሰብ በዓልን ከቤተሰብ ጋር መዋል ይናፍቀኛል፤ ነገር ግን ዙሪያዬን ስመለከት የሰላም አየር እየተነፈሰ የሚያልፈውን ሕዝብ እና በበዓል ደስታ የሚዝናናውን ማኅበረሰብ ስቃኝ ውስጤ በትልቅ እርካታ ይሞላል፤ የኔ ከቤተሰቤ መለየት የሺዎች ቤተሰቦች በሰላም እንዲሠበሠቡ፣ በዓልን በደስታ እና በፍቅር እንዲያሳልፉ መንገድ ይከፍታል፤ ይህ ነው ትልቁ የበዓል ደስታዬ” ይላሉ ምክትል ኢንስፔክተር መላኩ ገብሬ

የበዓሉ ዋዜማ ዕኩለ ሌሊት ሲደርስ እና ከተማዋ አዲሱን ዓመት በእልልታ ስትቀበል የምክትል ኢንስፔክተር መላኩ በዓል አከባበር ከባልደረቦቻቸው ጋር ሰላም ማስከበር ነው።

በበዓል ዕለት ከባልደረቦቻቸው ጋር የሚለዋወጧት አጭር መልዕክትም “እንኳን አደረሳችሁ፣ ቀጣናው ሰላም ነው!” የምትል ብቻ ናት።

እኛ በሞቀ ቤታችን አዲሱን ዓመት በሰላም እንድንቀበል ብርድ እና ዝናቡ ሳይበግራቸው የሌሊቱን ቁር የሚጋፈጡት እነዚህ የሰላም ዘበኞች የዘመናችን የጸጥታ ባለውለታዎች እና ባለታሪኮች ናቸው።

የሰላም አስከባሪዎች የሚከፍሉት መስዋዕትነት ፍሬ የሚያፈራው የሕዝቡ ትብብር ሲታከልበት ነው። ማኅበረሰቡ በበዓላት ወቅት ሰላምን በማስጠበቅ ረገድ የጸጥታ መዋቅሩ የቅርብ ተባባሪ እና የሰላም አምባሳደር ሊኾን ይገባል።

የምንደሰትበት ሰላም በሌሎች መስዋዕትነት የመጣ መኾኑን ተረድተን የአካባቢያችንን ሰላም በመጠበቅ እና ለጸጥታ አካላት አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ የሰላሙ ባለቤት እንሁን።

#አሚኮ #አዲስ_ዓመት #ሰላም_አስከባሪ_ዘቦች #አማራክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹

ባሕርዳር #መስከረም_01/2019_ዓ_ም

✍️ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleከዓመት ዓመት የሚናፈቁት፣ በልብ ውስጥም የማይጠፉት የአዲስ ዓመት ትዝታዎች።
Next article🌻 ከዓለም የምትለየው የ13 ወራት ባለቤቷ ኢትዮጵያ