🌻 ከዓለም የምትለየው የ13 ወራት ባለቤቷ ኢትዮጵያ

11

 

የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ከጎርጎሬሳውያኑ የቀን መቁጠሪያ በሰባት እና ስምንት ዓመታት ልዩነት አለው። የኢትዮጵያ የዘመን ቀመር አስራ ሁለቱንም ወራት ዕኩል 30 ቀናት አድርጎ 13ኛዋን ወር ጳጉሜን በማስከተሉ ልዩ የተፈጥሮ ሥርዓት እና የሥነ ፈለክ ጥበብ መገለጫ መኾኑ አስገራሚ ያደርገዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል የስበከተ ወንጌል መምህር መምህር ምኅረተአብ ክብር ስለጳጉሜን ሚስጥር እንዲህ ገለጹልን፡፡

ጳጉሜን የ5፣ የ6 እና የ7 ቀናት ርዝማኔ አላት። ከመስከረም 1 ቀን ጀምሮ እስከ ነሐሴ 30 ያሉት 12 ወራት እያንዳንዳቸው 30 ቀናት ያሏቸው ናቸው። አንድ ዓመት 365 ቀናት፣ 6 ሰዓት እና 0 ነጥብ 4 ደቂቃ የጊዜ ርዝማኔ ያለው በመኾኑ ከ360 የተረፈችው 5 ቀን ጳጉሜን ትፈጥራለች። 6 ሰዓታት ተጠራቅመው በ4 ዓመት 24 ይኾኑ እና አንድ ሙሉ ዕለት ይፈጥራሉ።

የቀረችው 0 ነጥብ 4 ደቂቃ ደግሞ በ600 ዓመት ተጠራቅማ ሌላ 7ኛ ቀን እንዲፈጠር ታደርጋለች። ስለዚህ የደቂቃ ሽርፍራፊዎች ሳይቀሩ ተሰልተው ኢትዮጵያን የ13 ወር ፀጋ ባለቤት እንድትኾን አስችለዋታል ነው ያሉት።

የሥነ ፈለክ ተመራማሪው መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶ.ር) የኢትዮጵያን የዘመን ቀመር ረቂቅነት ሲያስረዱ አንድ የፀሐይ ዓመት ሙሉ የሚኾነው በ365 ቀናት ከስድስት ሰዓት (15 ኬክሮስ) በመኾኑ የኢትዮጵያ የቀን መቁጠሪያ እነዚህን የሰዓት ሽርፍራፊዎች ቀምሮ በመያዝ የሚታወቅ ነው ይላሉ፡፡

የምዕራባውያን የዘመን አቆጣጠር እነዚህን ትርፍ ስድስት ሰዓታት በተለያዩ ወራት ላይ በመበተን እና በየአራት ዓመቱ የካቲት ወርን 29 ቀን በማድረግ የቀን መዛባትን ለማስተካከል ይሞክራል። የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ግን ትርፍ ሰዓታቱን ሳይበትን በራሷ በጳጉሜን ወር ላይ በጥንቃቄ ሠብሥቦ ይይዛቸዋል።

ለምን የጎርጎሮሳውያኑ ወራት 28፣ 29፣ 30 እና 31 ቀናት ያላቸው ኾነው የኢትዮጵያውያን ዘመን 12 ወራት በ30 በ30 ቀናት ተከፋፍለው ይቆጠራሉ ስንል መምህር ምኅረተአብን ለጠየቅናቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ኢትዮጵያውያን አባቶች ለቆጠራ የሚያገለግሏቸውን 9 ሺህ 900 የሃሳብ መስመሮችን በመጠቀም በሚሠራ ሒሳብ ምክንያት መኾኑን ያስረዳሉ።

3 ሺህ 300 ከሰሜን ወደ ደቡብ እና 6 ሺህ 600ው ደግሞ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ የተሰመሩ የሃሳብ መስመሮች ናቸው። እነዚህን መስመሮች ለ10 ሱባኤ በማካፈል የሚገኘው ቀሪ ወራትን 30 ቀናት እንዲይዙ ያደርጋቸዋል በማለት ገልጸዋል።

ሱባኤ የሚባለው 7 ቀን ነው። 10 ሱባኤ ማለት ደግሞ 7 በ 10 ሲባዛ ነው። ይህ ማለት 9ሺህ 900 ለ70 ሲካፈል 141 ደርሶ ቀሪው 30 ይመጣል። የቀረው 30 የወራትን ምጣኔ በቀናት የሚወክል እንደኾነ ገልጸዋል።

#አሚኮ #አዲስ_ዓመት #እንቁጣጣሽ #የዘመንቀመር #ኢትዮጵያ🇪🇹
ባሕር ዳር #መስከረም_01/2019_ዓ_ም

✍️በዘመኑ መኮንን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article🌻”ከቤተሰብ ማዕድ ይልቅ የሕዝብ ሰላም ይበልጣል” የሰላም ዘበኞቹ የበዓል መስዕዋትነት
Next article🌻”በበዓል ወቅት ሳይቀር በቁርጠኝነት መሥራታችሁ ለስኬት ያበቃችኋል” ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ