ከዓመት ዓመት የሚናፈቁት፣ በልብ ውስጥም የማይጠፉት የአዲስ ዓመት ትዝታዎች።

14
🌻
የክረምቱ ነጎድጓድ እና የወንዝ መሙላት አልፎ ምድር አበባን ስትጎናጸፍ፤ ጥቁሩ ዳመና አልፎ ሰማዩ ሲጠራ አሮጌው ዓመት አልፎ አዲሱ ዓመት ሲተካ ቤተሰብ፤ ጎረቤት፤ ዘመድ በአንድነት ተሠባሥበው አዲስ ዓመትን በኅብረት ያከብራሉ።
የአዲስ ዓመትን መምጣት ተከትሎ ጥቅም ላይ ያልዋሉ ዕቃዎች ሳይቀር ይታጠባሉ፤ ቤቱ በቀለም እና በተለያዩ ጌጦች ይደምቃል፤ ዶሮው፣ በጉ ይገዛል፤ ጠላው ይጠመቃል፤ ድፎው ይደፋል።
የጥዋቷ ጮራ ስትገለጥ ሕጻናት በአዲስ ልብሳቸው አጊጠው፤ አደይ አበባ ይዘው “እንቁጣጣሽ” እያሉ ይዞራሉ። ቤተሰብ የባሕል አልባሳትን ይለብሳል፤ ዶሮ እና በጉ ይታረዳል።
አልፎ አልፎም ለበዓሉ የተገዛ ዶሮ ጠፍቶ ፍለጋው ሲጧጧፍ፤ የበግ ስጋ በድመት ሲሠረቅ ማየት የበዓል ወቅት ትዝታ ናቸው።
ወለሉ በቄጤማ ተሞልቶ፤ እናቶች ዶሮ ወጥ ለመሥራት ሽር ጉድ እያሉ፤ የበዓል ሙዚቃ እየተሠማ፤ የተራራቁ ቤተሰቦች ተገናኝተው በገጠመኞቻቸው እየተሳሳቁ፤ የጭሱ መዓዛ ነብስን እያወደ አዲስ ዓመትን ያሳልፋሉ።
የተለያዩ ባሕላዊ ምግቦች ተሠርተው፤ የሩቅም የቅርብም ቤተሰብ ተሠባሥበው፤ ጠላው በዋንጫ፤ ጠጁ በብርሌ ቀርቦ፤ ሰላም፤ ፍቅር እና ዕድገት እየተመኙ በዓሉን ያደምቁታል።
ሸማግሌዎች በክብር ተቀምጠው የሕይወት ዘመን ገጠመኞቻቸውን እያወጉ፤ ዓመትን ከዓመት እያነጻጸሩ፤ በሕጻናት ተግባር የኋሊት እየተጓዙ ልጅነታቸውን ያስታውሳሉ።
ቁርስ፤ ምሳ፤ እራት ጎረቤት ከጎረቤት እየተጠራራ በየተራ ይበላል፤ የተጣሉ ለአዲስ ዓመት በይቅርታ ይታረቃሉ፤ ያለፈው ዓመት መልካም ሥራ እየተወሳ ይደነቃል፤ የገጠሙ ችግሮች ተነስተው ትምህርት ይወሰድባቸዋል።
ቤተሰብ በአንድነት ኾነው በአዲስ ዓመት ዕቅዳቸው ላይ ይመክራሉ፤ ሩቅ የነበሩ የቤተሰብ አባላት ያመጡትን ስጦታ ይሰጣሉ፤ ደስታ፤ ተስፍ እና ፍቅር በአንድነት ይገለጣሉ።
አዲስ ዓመት በኢትዮጵያ በባሕላዊ ትሥሥር ደምቆ፤ የገቢያ ድባቡ በኅብር ዜማ ፈክቶ፤ በመልካም ምኞት ታጅቦ፤ አንድነት እና ፍቅር ተሰብኮ፤ ሰለ ሀገር ሰላም ተጸልዮ፤ ማኅበራዊ ሕይወት የፍቅር ካባ ተጎናጽፎ፤ መተጋገዝ እና መረዳዳት በአደይ አበባ ውስጥ ፈክቶ በድምቀት ይከበራል።
ቁርጥ ስጋው ከጠጁ፤ ክትፎው ከብርዙ፤ ዶሮ ወጡ ከጠላው፤ ጥብሱ ከአረቂው፤ ጋኑ ከብርሌው ተዋህደው፤ ባሕላዊ አልባሳቱ በዐውደ ዓመት ኅብር ዜማ በእስክስታ ታጅበው ዓዲስ ዓመቱ በደስታ ይታለፋል።
ኢትዮጵያዊነት ኅብር፤ ውበት፤ መተሳሰብ፤ ፍቅር እና አንድነት መኾኑ በገሃድ ይታያል። በዓሉ በሽማግሌዎች ምርቃት፤ በልጆች ብሩህ ተስፋ፤ በእናቶች ጸሎት፤ በወጣቶች ምኞት፤ በማኅበረሰቡ ፍቅር እና አንድነት ጎልቶ፤ ለቀጣዩ ዓመት መልካም ምኞት በመመኘት ይጠናቀቃል።
የአዲስ ዓመት ትውስታዎን 💬 ያጋሩን
ባሕር ዳር #መስከረም_01/2019_ዓ_ም
✍️ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“ዘንድሮስ ሰላም በኾነልን” የእናት ጓዳ የናፈቃቸው ልቦች የአዲስ ዓመት ጸሎት
Next article🌻”ከቤተሰብ ማዕድ ይልቅ የሕዝብ ሰላም ይበልጣል” የሰላም ዘበኞቹ የበዓል መስዕዋትነት