
ኢትዮጵያ ከክረምቱ የውኃ ማዕበል እና ከጭጋጋማው የሰማይ ሥር የምትወጣበት፤ ነጭ ደመናዎች እንደ ጥጥ ተለቅመው በሰማዩ ሸራ ላይ የሚንሳፈፉበት፤ የማለዳ ፀሐይ በልዩ ሙቀት ከምድር የምትስማማበት እና ጋራ ሸንተረሩ በአደይ አበባ ወርቃማ ጸዳል የምትሞሸርበት ወርቃማ ወር መስከረም።
በዚህ ልዩ ወር ልክ እንደ ምድሪቱ ፍካት እና እንደ ሰማዩ ጥራት ሁሉ የኢትዮጵያውያን ልብም በተስፋ፣ በፍቅር እና በይቅርታ ይሞላሉ። አዲስ ተስፋ፣ አዲስ ገጽታ እና ልዩ መንፈሳዊ ድባብ በሰዎች ልብ ላይ ይነግሳሉ። ተቋርጠው የነበሩ ግለሰባዊ እና ማኅበረሰባዊ ግንኙነቶች ዳግም ይቀጥላሉ።
ዶፍ ሲያወርድ የነበረው ሰማይ ዝናቡ ሲቀንስ፤ ወንዞች ሲጎድሉ፤ ጭቃው ሲደርቅ እና መንገዱ ሲከፈት “መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ፥እንኳን ሰው ዘመዱን ይጠይቃል ባዳ” እያለ ተለያይቶ የሰነበተው ዘመድ፣ ጓደኛ በአዲስ የናፍቆት እና የተስፋ ስሜት ይጠያየቃል።
አዲስ ዓመት ከምንም በላይ የሩቅ ዘመድ የሚጠያየቅበት በዓል ነው። በተለይ አዲስ ዓመት ሰው እና ተፈጥሮ አብረው የሚታደሱበት፣ የደግነት እና የሕዝባዊ አንድነት ማሳያ ታላቅ በዓል ነው።
በኢትዮጵያ ምድር ተፈጥሮ መሠረቷን አትስትም። ልክ እንደ ሁልጊዜው ዘንድሮም መስከረም ሰማዩን ገልጦ፤ አደይ አበባ ምድሪቱን አሳምሮ ብቅ ብሏል። ሰውም በአዲስ ተስፋ እና ምኞት ተፈጥሮን ተቀብሏል።
ኾኖም ይህ በአዲስ ዓመት የሚታየው ድንቅ ባሕል ባለፉት ሦሥት ዓመታት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት ከባድ ጠባሳ አርፎበታል። መስከረም ሰማዩን ቢገልጥም፤ አደይ አበባ ምድሪቱን ብታስጊጥም ያልቆመው ግጭት በበዓሉ ላይ ጥቁር ጥላ መጣሉ አልቀረም። በዓመት በዓል ልጅ እናቱን እንዳይጠይቅ፤ ዘመድ ከዘመዱ እንዳይገናኝ በማድረግ ነባሩ ባሕል እንዲሸረሸር እያደረገም ይገኛል።
ግጭት፣ እገታ፣ ዝርፊያ እና ግድያ ትናንት በአዲስ ዓመት ዘመድ ፍለጋ ይጓዙ የነበሩ ብዙ እግሮችን ዛሬ የእናትን ደጅ እንዳይረግጡ አድርጓል።
ብዙዎች ከሩቅ ተሠባሥበው በአንድ ማዕድ መሰለፍን እንዲናፍቁ አድርጓቸዋል። የሕይወት ዘመን ምኞት እና ዕቅድ ቀርቶ “ሰላም” የሁሉም እንጉርጉሮ ከኾነም ሰነባብቷል።
ዛሬ የጀመርነው አዲስ ዓመት አሮጌውን ዘመን ወደ ታሪክ ማኅደር ቀብሮ አዲስ የብርሃን ምዕራፍ ይዞ መጥቷል።
ዛሬ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ የሚንቦገቦገው ትልቁ ምኞት አዲሱን ዓመት በአዲስ ልብስ ማጌጥ፤ በዓሉን በደስታ እና በፌሽታ ማሳለፍ ከድህነት ወጥቶ የሃብት ማማን መቆናጠጥ አይደለም። ይልቁንም የሁሉም ልብ እና አንደበት ጸሎት እና ምኞት በአንድ ቃል ላይ ቆሟል፥ እሱም “ሰላም” ነው።
ያ ከግጭቱ በፊት የነበረው ከቤተሰብ ርቆ የሚኖር ልጅ ወደ እናቱ ቤት ተጉዞ፤ ጎረቤት ከጎረቤት ተጠራርቶ ፤ ዘመድ ከባዕድ ሳይለያይ በአንድ የፍቅር ጥላ ሥር ይሠባሠብበት የነበረው የአዲስ ዓመት የባሕል ድባብ ያልናፈቀው እና ያልጓጓለት አንድም ነፍስ የለም። የግጭት አዙሪት አብቅቶ እና በመላ ሀገሪቱ ሰላም ሰፍኖ አዲሱን ዓመት ከናፈቁት ቤተሰብ ጋር ማሳለፍ ትልቁ ናፍቆት ኾኗል።
ወላጅ እና ልጅ አንድ ላይ የሚያሳልፉበት፤ ወጣቶች ያለስጋት በነፃነት የሚንቀሳቀሱበት፤ እማወራዎች በሀሴት ተውጠው ማዕድ የሚያዘጋጁበት ያ ወርቃማ ዘመን ዳግም እንዲመለስ ሕዝቡ በከፍተኛ ጉጉት ይጠባበቃል።
የእያንዳንዱ ሰው “ዘንድሮስ ሰላም በኾነልን” የሚል የልብ ትርታ እና ተስፋ ይዞ አዲሱን ዓመት ተቀብሏል።
ባሕር ዳር #መስከረም_01/2019_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
