
ኢትዮጵያ እጅግ የረቀቀ፣ የሥነ ፈለክ ጥልቅ ዕውቀትን መሠረት ያደረገ፣ ባሕረ ሀሳብን ከፀሐይ ዑደት ጋር ያስተሳሰረ፣ ከዓለም ቀደምት የኾነ ልዩ የዘመን አቆጣጠር ቀመርን ትከተላለች።
ከሌሎች ሀገራት የምትለይበት የ13 ወር ጸጋ ባለቤት ያደረጋት አንዱ ምክንያትም ይሄው ልዩ የዘመን አቆጣጠሯ መኾኑ ተመስክሮላታል።
የሥነ ፈለክ ተመራማሪው እና ደራሲ መጋቢ ሀዲስ ሮዳስ ታደሰ(ዶ.ር) እንደሚሉት ኢትዮጵያ ምዕራባውያን ሀገራት ከሚጠቀሙበት ከጎርጎሮሳውያን የዘመን ቀመር የተለየ የራሷ የዘመን አቆጣጠርን ትጠቀማለች።
የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ከምዕራባውያን አቆጣጠር የሰባት ወይም ስምንት ዓመታት ልዩነት እንዳለው ያብራራሉ። ይህ ልዩነት የመጣውም በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሮም በተነሳው በዲዮናስዮስ ኤክሲጉኦስ አማካኝነት ነው።
የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ከአውሮፓውያን በ7 ወይም 8 ዓመታት ወደ ኋላ መዘግየቱ የ365/366 ቀናት የፀሐይ ዑደት እና የቀደመውን የእስክንድርያ የ5ሺህ 500 ዓመተ ዓለም ስሌት በጥብቅ የመጠበቅ ውጤት ስለመኾኑ ይገልጻሉ።
በ4ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩት ቃሪያስ የተባሉ መነኩሴ ባደረጉት የሥነ ከዋክብት እና የመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን ስሌት ትክክለኛውን ቀመር ሠሩ። ይህንም ቀመር የኢትዮጵያ አባቶች ይህንን ስሌት በመቀበል እስከ ዛሬ ድረስ ይጠቀሙበታል።
ነገር ግን በ6ኛው ክፍለ ዘመን የተነሳው ዲዮናስዮስ ኤክሲጉኦስ የተባለ የሮም መነኩሴ ይህ አቆጣጠር ትክክል አይደለም ብሎ ቀመሩን እንደገና ማሥላት እንደጀመረ ያስረዳሉ።
ለቀመሩ ስሌት የተጠቀመውም 532 ዓመታትን ዓውደ ቀመር የትንሳኤ ሰንጠረዦችን፣ የሜቶኒክ ዑደቶችን ነበር። በዚህ ወቅት የክርስቶስን ልደት ስሌት እንደገና ሲያዘጋጅ የክርስቶስን የልደት ዓመት ከቃሪያስ (ከእስክንድርያ) ስሌት በ7 ዓመታት አስቀደመው።
በዚህ ጊዜ ይህንን የቀመር ስሌት ሲያሰላ በኢትዮጵያውያን እና በጎርጎሮሳውያን ዘመን አቆጣጠር መካከል የሰባት ዓመታት ልዩነት እንደተፈጠረ የዘመን ቀመር አዋቂዎች አስቀምጠውታል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ግን በቀደመው የዘመን ቀመር መሠረት ልደተ ክርስቶስን መነሻ አድርጋ ዓ.ም ብላ መቁጠር ጀምራለች። የሮማውያን ዲዮናስዮስ ኤክሲጉኦስ ደግሞ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን ላይ ኤ.ዲ ብሎ ጀምሯል ነው ያሉት።
በሁለቱ አቆጣጠሮች መካከል ያለው የዓመታት ልዩነት ዓመቱን ሙሉ 7 ዓመት ኾኖ አይቆይም።
እንደ መጋቢ ሀዲስ ሮዳስ ታደሰ(ዶ.ር) ማብራሪያ የእነዚህ 10 ዕለታት ልዩነት የመጣው ፖፕ ጎርጎርዮስ በወቅቱ የነበረውን የዘመን አቆጣጠር ማየት እና መከለስ አለብኝ ብለው የሮማውያንን የዘመን መቁጠሪያ
በ1582 ዓ.ም ከልሰው በተጠቀሙት የቀመር ስሌት ምክንያት የተፈጠረ ነው። ለዚህም ጥቅምት 4/1582 ዓ.ም ታሪካዊ ዕለት ናት ብለዋል።
በዚያች ዕለት ቀጣዩ ቀን ጥቅምት 5 መኾን ሲገባው ጥቅምት 15 ቀን መኾን አለበት ብለው የ10 ቀን ጭማሪ አድርገው መቁጠር እንደጀመሩ ያብራራሉ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የቀናት ልዩነት ተፈጠረ።
በዚህ ወቅትም በርካታ የዓለም ሀገራት ተቃውመዋቸው እንደነበር አንስተዋል። በሂደት በሮም ተጽዕኖ ስር የነበሩት ሌሎች ሀገራትም እየተቀበሉት መምጣታቸውን አስረድተዋል። በአሁኑ ወቀት የምዕራባውያን ሀገራት ይጠቀሙበታል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ግን የጥንት የዘመን ቀመር አቆጣጠር ሥርዓቷን ጠብቃ የፖፕ ጎርጎርዩስን የቀን ጭማሪ እና ዲዮናስዮስ ኤክሲጉኦስ የ7 ዓመታትን ጭማሪ ሳትቀበል ቀጥላለች ብለዋል። የቀደመውን የቀመር ስሌት እንዳጸናች ዘልቃለች።
ይህም ኢትዮጵያ የራሷ የኾነ ነጻ፣ ሙሉ እና የተደራጀ የቀን መቁጠሪያ ባለቤት እንድትኾን አድርጓታል። በዚህ የተነሳ “ኢትዮጵያ የዓለም ታሪክ ጠባቂ ናት” ይላሉ። 
ባሕር ዳር #መስከረም_01/2019_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
