እንቁጣጣሽ የፍቅር እና የተስፋ ስጦታ

6
🏵️🌻🌻
🌻እንቁጣጣሽ እንቁጣጣሽ
በየ ዓመቱ ያምጣሽ….
የዘመን መለወጫ ወይም እንቁጣጣሽ በዓል ሲከበር የክረምቱን ጨለማ፣ ዝናብ እና ደመና አልፎ ፀሐይ የሚወጣበት፣ ምድርም በአረንጓዴ ልምላሜ እና በእንቁጣጣሽ አበባ እንደ እንቁ የምታበራበት የምሥጋና እና የተስፋ ወቅት ነው።
🌻ታዲያ የዘመን መለወጫ በዓል እንቁጣጣሽ እንዴት ተባለ? በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ሥብከት የማኅበራት ማደራጃ ክፍል ኀላፊ ርእሰ ርኡሳን ቆሞስ አባ ኅይለ ማርያም ታገለ መሥከረም እንቁጣጣሽ የተፈጥሮ መታደስ በተለይም ምድር የክረምት ጨለማ ፣ ዝናብ እና ደመና አልፎ ፀሐይ የሚወጣበት እና ምድር በአረንጓዴ ልምላሜ እና በአበባ የምታሸበርቅበት የመጀመሪያ ወር ናት ይላሉ።
በቅዱስ መጽሐፍ እንደተገለጠው በኖህ ዘመን የነበረው የጥፋት ውኃ ጎድሎ ምድር ታየው፣ ኖህም ከመርከብ ወጥቶ መሥዋዕት ያቀረበበት እና ቀስተደመና የቃል ኪዳን ምልክት ኾኖ የታየው በዚህ ወር መጀመሪያ ነው። አባቶች ዘመናትን በማስላት ሲከፍሉ መስከረም አንድን የዓመት መጀመሪያ እንዳደረጉት ይገልጻሉ። በዚህም መሥከረም አንድ የዘመን መለወጫ ወይም እንቁጣጣሽ ይባላል።
ርእሰ ርኡሳን ቆሞስ አባ ኅይለ ማርያም ታገለ እንቁጣጣሽ የሚል ሥያሜ የተሰጠበትን እንዲህ ይገልጹታል። የኢትዮጵያ ንግሥት ንግሥተ ሳባ የንጉሥ ሠሎሞንን ጥበብ ለማየት ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘች። ከዚያም ንጉሥ ሠሎሞን ዕንቁ ለጣትሽ የሚኾን በማለት የከበረ እንቁ ወይም ጌጣጌጥ በስጦታ መልክ አበርክቶላታል። ንግሥቲቱ ወደ ሀገሯ የተመለሰችው በዚህ በመስከረም ወር ላይ በመኾኑ የሀገሯ መኳንንት እና መሣፍንቱም ዕንቁ ጣጣሽ (ለጣትሽ እንቁ) በማለት ተቀብለዋታል። በዚህ ሂደት “እንቁጣጣሽ” የሚለውን ስያሜ አግኝቷል ይላሉ።
ሌላው እንቁጣጣሽ ምድር በቢጫ አደይ አበባ ደምቃ እና አሸብርቃ እንደ ዕንቁ ታበራለች። መሥከረም ወር ክረምት አልፎ፣ ምድር በአደይ አበባ እና በተለያዩ ዕፅዋት የምታጌጥበት ወቅት ነው። በዚህ ወቅት አበቦች ሲፈነዱ እና ምድር ስታጌጥ ልክ እንደ “እንቁ” ስለምታበራ የተፈጥሮን ውበት ለመግለጽ የተሰጠ ስምም ነው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አሮጌው ዘመን አልፎ አዲሱን ዓመት ስትቀበል፤ ባለፈው ዓመት የነበረንን የአገልግሎት ውስንነት እና አለመግባባት በንስሐ፣ በይቅርታ እና በይቅርባይነት አስወግዶ ወደ እግዚአብሔር የሚቀረብበት ጊዜ አድርጋ ታስተምራለች ነው ያሉት።
በተለይም መጭው ዘመን የሰላም፣ የደስታ፣ የተሥፋ፣ የመተጋገዝ፣ የፍቅር እና የአንድነት እንዲኾንም በመመኘት ጸሎት የሚደረግበት ነው ብለዋል።
የክረምቱ መከራ እና ከውኃ ሙላት አልፎ መስከረም ሲመጣ፣ የሰው ልጅ በነፃነት የሚንቀሳቀስበት፣ አዲስ ተስፋ የሚሰንቅበት እና የዓመት ዕቅዱን የሚጀምርበት ወቅት ነውም ይላሉ።
​ይህ ወር ያረጀውን አስተሳሰብ አስወግደን በአዲስ መንፈስ የምንነሳበት፣ የተቸገረውን የምንረዳበት እና በሰላም እና በፍቅር በነፍስ እና በሥጋ የምንከብርበት የተባረከ ዘመን እንዲኾን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
መልካም በዓል!🌻🌻🌻
ዘጋቢ:-ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleመስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ፣ እንኳን ሰው ዘመዱን ይጠይቃል ባዳ። እንቁጣጣሽ እንኳን መጣሽ፤