መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ፣ እንኳን ሰው ዘመዱን ይጠይቃል ባዳ። እንቁጣጣሽ እንኳን መጣሽ፤

4
🏵️
በአበቦች መሐል እንምነሽነሽ። የሚለው ኅብር ዜማ ሲሰማ በሁሉም ልብ ላይ ልዩ ስሜት ይቀሰቀሳል። ንጋቱን ሊያበሥሩ ዶሮ እና አዕዋፋት ሲጮሁ የአዲስ ዓመት ንጋትን ለማየት በአዲስ መንፈስ ሁሉም ይነሳል።
ሕጻናት አዲስ የተገዛላቸውን ልብስ ለብሰው፤ የአደይ አበባን 🏵️ እና በወረቀት ያሳሉትን እንቁጣጣሽ ይዘው በማለዳ የወዳጅ ዘመዶቻቸውን በር አስከፍተው እንኳን አደረሳችሁ ይላሉ፤ በየ መንገዱም በኅብረት ይጓዛሉ።
ዘመድ ተሠባሥቦ፤ ጠላው ተጠምቆ፤ ዳቦው ተጋግሮ፤ በሕጻናት ዜማ ታጅቦ፤ የቡና ረከቦቱ ቀርቦ፤ በጭሱ መዓዛ የአዲስ ዓመት ተስፋ ተምጎ፤ ትንሽ ከትልቁ በአንድ መዓድ ቀርቦ በእኩልነት እየተበላ በደስታ ይታለፋል።
አዲስ ዓመትን ከሚያደምቁ ክዋኔዎች ውስጥ ባሕላዊ ሙዚቃዎች ልዩ ቦታን ይይዛሉ። በየመንገዱ፤ በየቤቱ የሚለቀቁ ባሕላዊ የዓውደ ዓመትን ሙዚቃዎች አብሮነትን፤ ሰላምን፤ ፍቅርን እና መልካም ምኞትን ይገልጻሉ።
✅የበዓል ሙዚቃዎች መልዕክት
🏵️ አብሮነትን መግለጽ እና ማስተሳሰር
መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ፣
እንኳን ሰው ዘመዱን ይጠይቃል ባዳ። ሲሉ በግጥሞቻቸው ውስጥ በዓላት የስጋ ዘመድን ከመጠየቅ ባለፈ የስጋ ዝምድና የሌላቸው ወገኖችን መጠየቅ እንደሚገባም ያመላክታሉ።
አብሮነት በስጋ ዝምድና የተከለለ ብቻ ሳይኾን ሁሉም በአንድነት የሚቆምበት፤ ኅብረት የሚጠነክርበት፤ መተጋገዝ እና መጠያየቅ የማኅበራዊ እሴት መገለጫ መኾኑን ያሳያሉ።
🏵️ ፍቅር እና ሰላም ይሰብካሉ
የጎመን ድስት ይውጣ፤
የገንፎ ድስት ይግባ፤
ሰላም ፍቅር ይዘህ ና መስከረም ጥባ። በማለት ደግሞ ሰላም እና ፍቅርን በግጥሞቻቸው ያስተምራሉ። የሀገር ሰላም እንዲረጋገጥ፤ ፍቅር እና አንድነት እንዲጎለብት፤ ችግሮች ተወግደው ሰላም እና ልማት በሀገር እንዲስፋፋ ምኞታቸውን ይገልጻሉ።
🏵️ ደስታ እና ዕድገት እንዲኾን ይመኛሉ
የሰላም የጤና የደስታ ይሁን፤
አዲሱ ዓመት አዲሱ ዘመን፤
ዕድገት ብልጽግና ይዞ ይምጣልን፤ በማለት በዓሉን በደስታ ማሳለፍ፤ ለሀገር ደግሞ ሰላም እና ዕድገት መመኘት እንደሚገባ በዜማዎቻቸው ይገልጻሉ።
ፍቅር ካለ ሰላም፤ ደስታ ካለ አብሮነት፤ ኅብረት ካለ ደግሞ ዕድገት እንዳለ በግጥሞቻቸው ይዘት እና በውብ ድምጻቸው ያስተጋባሉ።
የዐውደ ዓመት ዜማዎች ዘፈን ብቻ አይደሉም። እንደ አብሮነት፤ መተሳሰብ፤ አንድነት፤ ሰላም እና ፍቅር ያሉ መልዕክቶች የሚተላለፉባቸው፤ በተግባር እንዲገለጡ የሚመላከትባቸው ድንቅ ጥበብ እንጅ።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየእንቁጣጣሽ ብስራት – በአበባ ተጀምሮ በተስፋ የሚቋጭ የልብ ዜማ
Next articleእንቁጣጣሽ የፍቅር እና የተስፋ ስጦታ