የእንቁጣጣሽ ብስራት – በአበባ ተጀምሮ በተስፋ የሚቋጭ የልብ ዜማ

4
🌼
✨
ክረምቱ ሸሽቶ ሰማዩ ፊቱን ሲያጠራ ምድሪቱ በቢጫ የአደይ ግምጃ ስትዋብ የዘመኑ የመጀመሪያ ብስራት አብሳሪዎች ሕጻናት ናቸው። የማለዳ ጀንበር ስትወጣ ልጆች ገና በጠዋቱ የጤዛ ጠብታ ሳይረግፍ ወደ ተራራ እና መስክ የሚያደርጉት ጉዞ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር የሚያደርገውን ንጹሕ ግንኙነት ያሳያል።
ሕጻናቱ አደይ አበባ ሲሠበሥቡ አበባውን ብቻ ሳይኾን የዘመኑን አዲስ ተስፋ፣ ብርሃን እና ደስታ በእጆቻቸው ይዘው ይመለሳሉ። በልጆቹ የንጽሕና ዓለም ውስጥ ያች ጊዜዋን ጠብቃ የምትፈነዳ ቢጫ አበባ ከወርቅ የከበረች የፍቅር ስጦታ ኾና ከቤት ቤት እየዞሩ “እንቁጣጣሽ፤ እንኳን አደረሳችሁ!” በማለት የደስታ ዜማቸውን ያሰማሉ። ይህ የክረምቱን ጨለማ ገፎ የብርሃንን መምጣት የሚያበስር የነፍስ ዜማ ነው።
በገጠሩ በተለይም በጎጃም አካባቢ አዲስ ዓመት በእንግጫ እና ከሴ አጨዳ ይከበራል። ይህ ክዋኔ በዋናነት በልጃገረዶች የሚከወን ሲኾን የአዲስ ዓመት ማለዳ በየቤቱ እየዞሩ የተጎነጎነውን እንግጫ ለእንኳን አደረሳችሁ በስጦታ ያበረክታሉ። ይህ እንግጫ በቤቱ ምሶሶ እንዲታሰር ይደረጋል።
የሚለበሰው የሀገር ባሕል ያውም ነጭ አልባስ ነው፤ ይህም አዲሱን ዓመት በንጹሕ ልቦና የመቀበል የብሩህ ተስፋ ምልክት ተደርጎ ይቆጠራል።
በከተሞች አካባቢም ወንዶችም ሴቶችም በራሳቸው የተሳሉ ስዕላትን ወይም ጽሑፎችን በየቤቱ እያንኳኩ እንኳን አደረሳችሁ በማለት ያድላሉ፤ የሚሰጣቸው ምላሽም ምርቃት አሊያም ገንዘብ ሊኾን ይችላል።
ልጆቹ ያንን የተቀደሰ የተፈጥሮ ወይም መልካም ምኞት ጽሑፎችን አሊያም ስዕላትን በስጦታ ሲያበረክቱ ትላንትናን ከነገ ጋር የሚያስተሳስር መንፈሳዊ ድልድይ እየዘረጉ ነው። ቤቱ በአበባው ሽታ እና በልጆቹ ጫጫታ ሲሞላ አዲስ ሕይወት ወደ ቤቱ የገባ ያህል ይቆጠራል።
አባወራው እና እማወራው አበባውን በፈገግታ ሲቀበሉ የሚገቡት ቃል ደግሞ የዚሁ ውብ መስተጋብር ማሳረጊያ ነው፤ ከዓመት ቢያደርስን ብለው ለልጅ የሚኾን ስጦታ በሽልማት ለማበርከት ቃላቸውን ይሰጧቸዋል። ይህ ተራ የተስፋ ቃል ሳይኾን በጥልቅ ሲታይ ትልቅ የሥነ-ልቦና እና የባሕል እሴት ያለው ምርቃት ነው።
“ከዓመት ቢያደርስን” የሚለው ቃል የሰው ልጅ ለሕይወት ያለውን ጉጉት፣ ፈጣሪን ማመስገን እና የነገን ፀሐይ ለማየት ያለውን መሻት ያንጸባርቃል። “ሰላም ቢያደርሰን” ብለው ቀጣይ የሚመኙትም የኑሮ መሻሻልን፣ የተትረፈረፈ ማዕድን እና የነገን ብሩህ ተስፋ ለልጆቹ በምናባቸው እንዲስሉ የሚያደርግ የአባቶች እና የእናቶች ሕያው ጸጋ ነው።
የልጆች ስጦታ እና የወላጆች የተስፋ ቃል መለዋወጥ፣ ማኅበረሰባዊ መተሳሰብን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳይ አሻራ ነው። ልጆቹ ያለፈውን ዓመት የክረምት ጭቃ እና ድካም በአበባው ውበት ሲያብሱ አዋቂዎቹ ደግሞ የልጆቹን ነገ በተስፋ ቃል ይጠግባሉ። የእንቁጣጣሽ ጥልቅ ሚስጥርም ይሄው ነው፤ በአበባ ተጀምሮ፣ በተስፋ የሚቋጭ የልብ ዜማ።
ባሕር ዳር #መስከረም 01/2019 ዓ.ም
በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleእንቁጣጣሽ እና ልጆች
Next articleመስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ፣ እንኳን ሰው ዘመዱን ይጠይቃል ባዳ። እንቁጣጣሽ እንኳን መጣሽ፤