እንቁጣጣሽ እና ልጆች

6
🌻
🌻
ኢትዮጵያ የራሷ የዘመን መቁጠሪያ እና ከዓለም በተለየ በዓመት ውስጥ 13 ወራት ያሏት ድንቅ እና ልዩ ሀገር ናት።
ታዲያ በተለየ የቀን መቁጠሪያዋ አዲስ ዓመት የሚከበረው የክረምቱ ወቅት ማለቂያ እና የፀደይ ጊዜ መድመቂያ በኾነው መስከረም 1 ቀን ነው።
የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት እንቁጣጣሽ በሚለው ስሙ ይታወቃል። ስለእንቁጣጣሽ ስናስብ በሁሉም ሰው ልብ ውስጥ አዲስ ዓመት፣ አዲስ ተስፋ እና ብሩህ ነገርን የሚያስታውስ ነው።
🌻ዕንቁጣጣሽ እና የልጆች ትስስር ዕንቁጣጣሽ በተለይ በኢትዮጵያ ልጆች የምትናፈቅ እና በጉጉት የሚጠብቋት ናት። በተለይም በቀደመው ጊዜ ልጆች አዲስ ልብስ የሚገዛላቸው በአዲስ ዓመት በመኾኑ ቀኗን ይናፍቁታል።
ቀደም ብሎ ልብሱ ተገዝቶ ከኾነም የሚለበሰው የእንቁጣጣሽ ዕለት ስለኾነ ቀኑም አይሄድላቸውም፤ ሌሊቱም አይነጋላቸውም። አንዳንዴም በዋዜማው ምሽት የተገዛውን አዲስ ልብስ እና ጫማ ለብሰው የሚተኙ ልጆችም አይጠፉም።
🌻ዕንቁጣጣሽ እና ትውስታ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ የኾኑት ወይዘሮ ዘመናይ ከፍያለው በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል ተወልደው ማደጋቸውን ነግረውናል።
ስለ እንቁጣጣሽ ሲነግሩን በልጅነታቸው እንቁጣጣሽ በጣም የሚናፍቁት በዓል እንደነበር ነግረውናል። “የፍልሰታ ጾም ካለቀ በኋላ ለእንቁጣጣሽ የቀሩ ቀናትን በየቀኑ እንቆጥር ነበር” ብለዋል። ምክንያቱ ደግሞ እንደከተማ ልጆች ባይኾንም አዲስ ልብስ ይገዛልናል፤ ከጓደኞቻችን ጋር እንጫወታለን ነው ያሉት።
በዋዜማው ልጆች ተሠባሥበው አደይ አበባ ለመቁረጥ ወደ ሜዳ ይሄዳሉ፤ አደይ አበባ እና ሰበዝ የሚመስል ሳር በመቁረጥ አንድ ላይ ይጎነጎናሉ፤ ከዚያም በማግስቱ በየሰው ቤት በመሄድ እንቁጣጣሽ እያሉ የተጎነጎነውን አበባ በስጦታ መልክ እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል።
ስጦታውን የሚቀበሉ እናቶች እና አባቶችም እንቁጣጣሽ ሲባሉ በየዓመቱ ያምጣችሁ ብለው እንደሚመርቁ ነው የገለጹት።
በስጦታም ዳቦ እንደሚሰጡ አንስተዋል። በእሳቸው ዘመን ገንዘብ በስጦታ እንደማይሰጥም ነግረውናል። ልጆችም በዚህ መልኩ ሁሉንም የሰፈር ሰው አዳርሰው በኋላም ተሠባሥበው ሜዳ ላይ ይጫወቱ እንደነበር የረጅም ጊዜ ትዝታቸውን አካፍለውናል።
የወይዘሮ ዘመናይ ልጅ ሔርሜላ ጌታቸው የተወለደችው እንደእናቷ በገጠር ሳይኾን በከተማ ነው። ሔርሜላ ጌታቸው አሁን ላይ ስለእንቁጣጣሽ አሚኮ ጠይቋት የእንቁጣጣሽ በዓልን እደምትወደው ተናግራለች።
ምክንያቱም “አዲስ ልብስ እና ጫማ ይገዛልናል፣ ጸጉራችን እንሠራለን፣ በግ ይገዛል” ስትል ይህ ሁሉ እንደሚያስደስታት ገልጻለች።
ዝግጅቱን በተመለከተ እንቁጣጣሽ ከመድረሱ ቀናትን ቀደም ብለው ልጆች በወረቀት ላይ የተለያዩ አበቦችን ሥዕል እንደሳሉም ነው ያብራራችው።
የበዓሉ ዕለትም አዲሱን ልብስ ለብሳ በጎረቤት እና ከዘመድ ቤት በመሄድ እንቁጣጣሽ በማለት በወረቀት ላይ የሳለችውን ሥዕል በስጦታ እንኳን አደረሳችሁ ዕንቁ ጣጣሽ እያለች እየሰጠች እንደኾነም ተናግራለች።
ስጦታውን የሚቀበሉ እናቶች እና አባቶችም እንቁጣጣሽ ሲባሉ በየዓመቱ ያምጣችሁ ብለው ዳቦ ከሌለም የገንዘብ ስጦታ እየሰጧቸው ስለመኾኑ ጠቁማለች። እንቁጣጣሽ ብለው ባገኙት ገንዘብ ለተለያዩ ቁምነገሮች እንደሚያውሉትም ነግራናለች።
ከእናት እና ከልጅ በዓል አከባበር የተረዳነው በዓሉ በፊትም አሁንም የሚከበር መኾኑን እና በተለይም ደግሞ እንቁጣጣሽ በልጆች ዘንድ ተወዳጅ መኾኗን ነው።
በከተሞች አሁንም ቢኾን አበባየሁሽ የሚጨፍሩ እንኳን አደረሳችሁ የሚሉ በርካታ ሴት ሕጻናትን ድምጽ አሚኮ መስማት ችሏል።
እነዚህም በተመሳሳይ ዳቦ እና የገንዘብ ስጦታ ይበረከትላቸዋል። ልጆችም በምላሹ ከብረው ይቆዩን ብለው ለቀጣይ ዓመት በሰላም እንዲደርሱ መልካም ምኞታቸውን በዜማ ሲገልጹ ታዝበናል።
መልካም አዲስ ዓመት!🌻
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየኢትዮጵያ የዘመን ሳይንስ!
Next articleየእንቁጣጣሽ ብስራት – በአበባ ተጀምሮ በተስፋ የሚቋጭ የልብ ዜማ