የኢትዮጵያ የዘመን ሳይንስ!

14
ተስፋን ሰንቄ እና የአዲስ ዓመት መዳረሻን ተንተርሼ የሀገሬን የረቀቀ የዘመን ቀመር ልዩ ባሕርይ ለመጠየቅ ወደ ባሕር ዳር ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል አመራሁ።
ወደ ካቴድራሉ ግቢ በገባሁበት ሰዓት የቤተክርስቲያን ሊቆችን ስለ ዘመን ቀመር ሲመራመሩ ቆይተው ከትልቅ አዳራሽ ሲወጡ ደረስኩ። እኔ እፈልጋቸው የነበሩ መምህር ደግሞ ከአንድ ጥግ ከሌላ የዘመን ቀማሪ አባት ጋር ስለ አንድ የዘመን ቀመር ስሌት ጠንከር ያለ ጥያቄ እና መልስ እያደረጉ ነበር። ውሥብሥብ የኾነን የዘመን ቁጥር እስክሪብቶን ከወረቀት ሳያዋህዱ በቃል ብቻ ሲደምሩ ሲቀንሱ ስመለከት የባይተዋርነት ስሜት ቢሰማኝም የመጣሁበትን ጉዳይ በተመለከተ በቂ መልስ ላገኝበት የምችልበት ትክክለኛ ቦታ እንደመጣሁ ተሰማኝ ።
በሰላምታም ቢኾን ላቋርጣቸው አልፈለግኩም መቋጫቸው ምን ይኾን የሚል ጥያቄ ውስጤ ላይ ፈጥሬ እከታተላቸው ጀመር። ለመግባባት እና ለመረዳዳት ቢኾንም የሚያነሱት ጥያቄ እና የሚሰጡት መልስ ብርቱ ኀይል አለው። ጆሮቼ እስከቻሉት በትዕግስት ተከተሏቸው።
በመጨረሻም ለመጣሁበት ጉዳይ የቀጠርኳቸው መምህር በረቀቀ መንገድ የዘመን ቅመራውን ሠርተው በማሳየት መግባባት ላይ ደርሰው የሁለቱ ግንኙነት በምሥጋና ሲቋጭ ለመምህሩ ምልክት ሰጠኋቸው እና ቀረብ ብለን ሰላምታ ተለዋውጠን ወደ ጣና ሐይቅ አቅጣጫ እየተራመድን እግረ መንገዳችንም ስለመጣሁበት ጉዳይ እያስረዳኋቸው በሐይቁ ዳርቻ ደረስን፣ አንድ ጥግ ላይ ተቀመጥን እና ጨዋታችንን ጀመርን።
መምህሩ ለዓመታት በጣና ሐይቅ ክብራን ገብርኤል አንድነት ገዳም ደሴት ካሉ አባት ባሕረ ሃሳብን እና አቡሻክርን የተማሩ ሲኾን ለዓመታት የቀሰሙት ዕውቀት እና ጥበብ ለትውልድ ይተርፍ ዘንድ ደግሞ በቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል የባሕረ ሃሳብ እና የአቡሻክር ትምህርትን እያጋሩ ይገኛሉ። በካቴድራሉ የወንጌል መምህርም ናቸው – መምህር ምኅረተአብ ክብር።
ለጨዋታችን መጀመሪያ ይኾን ዘንድ በዓለማችን በርካታ ሀገራት የራሳቸውን የዘመን ቀመር በተለያየ መሠረት እና መነሻ ቀምረው ሲቆጥሩ እንደኖሩ ከእነዚህም ውስጥ ጥንታዊት ሮም፣ ግብጽ እና ሌሎችም የሚጠቀሱ መኾኑን ገለጹልኝ።
ኢትዮጵያ ከሌሎቹ በተለየ ሁኔታ መተንተን፣ መገለጽ፣ መተርጎም እና በአመክንዮ መደገፍ የሚችል የራሷ የኾነ የዘመን ቀመር ያላት ሀገር ናት። ምዕራባውያን እና አውሮፓውያን ከሚቆጥሩበት የዘመን ቆጠራ 7 ወይም 8 ዓመታት ወደ ኋላ የቀረ የሚመስል ነገር ግን የአመክንዮ መሠረት ያለው፣ የዘገየ ሳይኾን ዕውነት የኾነ፣ ኋላቀር ሳይኾን የረቀቀ ውሥብሥብ የሒሳብ ስሌት ያለው ፣ ከተፈጥሮ እና ከሰው ልጅ ሕይወት ጋር የተሳሰረ ነው – የኢትዮጵያ የዘመን ቆጠራ።
ሠለጠኑ የሚባሉ ሀገራት የሚጠቀሙበት የጎርጎሮሳውያን የዘመን አቆጣጠር ለምን ከኢትዮጵያውያን ተለየ በማለት ለጠየቅኳቸው ጥያቄ ልዩነቱ የተፈጠረው በ1582 ዓ.ም ጎርጎሪዎስ ሳል በሚባል ሰው እንደነበረ ገለጹልኝ።
የጁሊያን ዘመን አቆጣጠር ችግር አለበት በማለት ከኒቂያ ጉባኤ ማለትም ከ325 ዓ.ም ጀምሮ በመቁጠር 10 የተገደፉ ወይም ያልተቆጠሩ ቀናት መኖራቸውን ጎርጎሪዎስ በማረጋገጣቸው በነጋታው ኦክቶበር 5 መኾን እያለበት 10 ቀን በመጨመር ኦክቶበር 15 ተብሎ እንዲቆጠር በአዋጅ ማስነገራቸውን አጫወቱኝ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ተዘለሉ የተባሉ የቀናት፣ የሰዓታት፣ የደቂቃዎች እና የሴኮንድ ሽርፍራፊዎች ተደማምረው ከ7 እስከ 8 ዓመት ልዩነት ፈጠሩ በማለት ታሪኩን በአጭር አስረዱኝ።
እንደ መምህሩ ገለጸ ጎርጎሪዎስ በአዋጅ የቀን ለውጥ ሲያደርግ ሕዝቡ ከዕድሜያችን ላይ ጨመረብን በማለት ተቃውሞ አሰምቶ እንደነበረም ታሪክ ጠቅሰውልኛል።
የኢትዮጵያ የዘመን ቀመር ከሥነ ፍጥረት የሚጀምር እና ተፈጥሮን መሠረት የሚያደርግ ነው። አባቶቻችን የፀሐይን፣ የጨረቃን እና የከዋክብትን ዑደት በማጥናት ሽርፍራፊ ሴኮንዶች እንኳን ሳይቀር በተጨባጭ ምክንያት ተደግፈው ዘመንን ይቆጠራሉ። እነዚህን ፍጥረታት በመጠቀም የሚቆጥሩበትን የዘመን ቀመር በሥርዓት ሰንደው የያዙ የባሕረ ሃሳብ እና የአቡሻክር መዛግብት አሉ።
ከሥነ ፍጥረት ጅማሮ እስከ ሥነ ፍጥረት ፍጻሜ ያለውን ጊዜ የሚቀምሩ፣ የኖሩትን ብቻ ሳይኾን ያልኖሩትን ጭምር መቁጠር እና በዘመናት ውስጥ ያሉ ክስተቶችን በተጨባጭ መተንበይ የሚችሉ ኢትዮጵያውያን አባቶች የኖሩበትን የዘመን ቅመራ ዕውቀት በዘመን ጎዳና አሻግረው ዛሬም ድረስ ያሉ ጥቂት ብሩህ አባቶች የተረከቡትን ጥበብ በአደራ እየተራቀቁበት ይገኛሉ።
መምህር ምኅረተአብ ኢትዮጵያውያን ዘመናትን በሰባት ዑደት እየሰፈሩ ለቆጠራ የሚጠቀሙ መኾኑን ገለጹልኝ። በሥያሜም ዐውደ ዕለት ( የ24 ሰዓት የጊዜ ዑደት)፣ ዐውደ ወርኅ (የ30 ዕለታት ዑደት)፣ ዐውደ ዓመት ( የ1 ዓመት የጊዜ ዑደት)፣ ዐውደ አበቅቴ ( የ19 ዓመት ዑደት)፣ ዐውደ ፀሐይ ( የ28 ዓመት ዑደት)፣ ዐውደ ማኅተም (የ76 ዓመት ዑደት እና ዐውደ ቀመር (የ532 ዓመት ዑደት) በማለት ዘረዘሩልኝ። በፀሐይ፣ በከዋክብት እና በጨረቃ ዑደት የሚለኩ ሰባቱ ዑደት ናቸው።
ከእነዚህ መስፈሪያዎች በተጨማሪ ኀምሲት፣ ራብኢት፣ ሣልሲት፣ ካልኢት እና ኬክሮስ የሚባሉ የጊዜ ክፍልፋዮችም ለቆጠራ አገልግሎት እንደሚውሉ አብራርተዋል።
የጎርጎሮሳውያን ዘመን ወራቶቻቸው 28፣ 29፣ 30 እና 31 ቀናቶች ያላቸው ሲኾን የኢትዮጵያውያን ዘመን ግን 12 ወራት በ30 በ30 ቀናት ተከፋፍለው ይቆጠራሉ። ይህ ለምን እንደኾነ መምህር ምኅረተአብ ሲያስረዱ ኢትዮጵያውያን አባቶች ለቆጠራ የሚጠቀሙባቸው 9 ሺህ 900 የሃሳብ መስመሮችን በመጠቀም በሚሠራ ሒሳብ ምክንያት መኾኑን አስረዱኝ። 3 ሺህ 300 ከሰሜን ወደ ደቡብ እና 6 ሺህ 600ው ደግሞ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ የተሰመሩ የሂሳብ መስመሮች ናቸው።
እነዚህን መስመሮች ለ 10 ሱባኤ በማካፈል የሚገኘው ቀሪ ወራቶቻችን 30 ቀናቶች እንዲይዙ ያደርጋቸዋል በማለት ገልጸዋል። ሱባኤ የሚባለው 7 ቀን ሲኾን 10 ሱባኤ ማለት ደግሞ 7 በ 10 ሲባዛ ነው። ይህ ማለት 9ሺህ 900 ለ70 ሲካፈል 141 ደርሶ ቀሪው 30 ይመጣል። የቀረው 30 የወራትን ምጣኔ በቀናት የሚወክል ነው።
በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ልዩ እንደኾነች የሚነገርላት ወር ደግሞ ጷጉሜን ናት። የ5 የ6 እና የ7 ቀናት ርዝማኔ አላት። ከመስከረም 1 ቀን ጀምሮ እስከ ነሐሴ 30 ያሉት 12 ወራት እያንዳንዳቸው 30 ቀናት ያሏቸው ቢኾንም አንድ ዓመት 365 ቀናት፣ 6 ሰዓት እና 0 ነጥብ 4 ደቂቃ የጊዜ ርዝማኔ ያለው በመኾኑ ከ360 የተረፈችው 5 ቀን ጳጉሜን ትፈጥራለች።
6 ሰዓታት ተጠራቅመው በ4 ዓመት 24 ይኾኑ እና አንድ ሙሉ ዕለት ይፈጥራሉ። የቀረችው 0 ነጥብ 4 ደቂቃ ደግሞ በ600 ዓመት ተጠራቅማ ሌላ 7ኛ ቀን እንዲፈጠር ታደርጋለች። ስለዚህ የደቂቃ ሽርፍራፊዎች ሳይቀሩ ተሰልፈው ኢትዮጵያን የ13 ወር ፀጋ ባለቤት እንድትኾን አስችለዋታል በማለት የጷጉሜን ምስጢር ነገሩኝ።
ከአውሮፓውያን በተለየ ኹኔታ የኢትዮጵያ የወራት እና የዕለታት ሥያሜም ከተፈጥሮ እና ሥነ ፍጥረት ጋር የተቆራኘ መኾኑን መምህሩ ያስረዳሉ። እሑድ የሥነ ፍጥረት መጀመሪያ ፣ የዕለት አንደኛ ነው፣ ሰኞ የፍጥረት ሁለተኛ ቀን እያለ እስከ ፍጥረተ ዓለም መቋጫ ቀን ቅዳሜ ይደርሳል።
ወራትንም ካየን ከኢትዮጵያ ማንነት ጋር የተቆራኘ ሀገራዊ መሠረት ያለው ነው። መስከረም ክረምቱ የሚወጣበት የመልካም ጊዜ እና የሐዲስ ኪዳን ምሳሌ ነው። ጥቅምት ደግሞ ጠቀመ፣ ሠራ እና ገነባ ማለት ሲኾን የአዝመራ መሠብሠቢያ ጊዜ በመኾኑ የላብ ዋጋ የሚገኝበት፣ የምንጠቀምበት ጊዜን እንደሚያመለክት እና ሁሉም ወራት እንዲህ ዓይነት ትርጉም ያላቸው እና ምክንያታዊ ናቸው ይላሉ መምህሩ።
ይህን ሁሉ ጨዋታ ስንጨዋወት የረፋዱ ጊዜ አልፎ ኖሮ የጣና ሐይቅ ማዕበል ወደ ዳርቻው መፈንጠቅ ጀምሯል። ፍንጣቂው ሲረጨን ከትኩረታችን ረገብ አልን እና የጣና ውበት ያሸነፈን በሚመስል ኹኔታ ቀልባችን መለስ ብሎ ወደኛ አቅጣጫ የሚመጣው ነፋስ የጣናን ውኃ በዳርቻ ከሚገኘው ድንጋይ ጋር እያጋጨ የሚፈጥረውን ውበት መመልከት ጀመርን። ጣና የጥበብ እና የውበት መፍለቂያ መኾኑን አስተዋልኩ። መምህርን አመሥግኘ በመጣንበት ሁለታችንም ተመለስን።
ባሕር ዳር #መስከረም 01/2019 ዓ.ም
✍️በዘመኑ መኮንን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleዕንቁጣጣሽ-የሰላም ፍኖት 🌻
Next articleእንቁጣጣሽ እና ልጆች