
ጳጉሜን 5 የነገው ቀን በአማራ ክልል ተከብሯል። ቀኑን የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ፣ የአማራ ክልል ሥራ እና ክህሎት ቢሮ፣ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ፣ የአማራ ክልል የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ እና የአማራ ክልል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ናቸው በጋራ ያዘጋጁት።
በመመርሐ ግብሩ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ወገኖች ለበዓል መዋያ ማዕድ የማጋራት፣ የዐውደ ርዕይ እና የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ሲቪል ሠርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኀላፊ ባንቺአምላክ ገብረ ማርያም የጳጉሜን ቀናት በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ልዩ ቦታ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ከአንድ ዓመት መጠናቀቅ እና ከአዲስ ዓመት መጀመር መካከል የሚገኙ የሽግግር ቀናት በመኾናቸው ሰዎች በእነዚህ ቀናት ያለፈውን ዓመት በመመልከት የተሠሩ ሥራዎችን፣ የተገኙ ውጤቶችን፣ ያጋጠሙ ችግሮችን እና የተገኙ ትምህርቶችን ትምህርት በመውሰድ ለመጭው አዲስ ዓመት በአዲስ ተስፋ መነሳሳት እና ለላቀ ውጤት የሚተጉባቸው ጊዜያት መኾናቸውን አንስተዋል።
መንግሥት የጳጉሜን ቀናት የወል ትርክት እና የሀገር መንግሥት ግንባታ መሠረት የኾኑትን የኢትዮጵያን ባሕል፣ ጥበብ እና ማኅበራዊ እሴቶች በማጎልበት ዜጎች ስለሀገራዊ እሴቶች የበለጠ እንዲያውቁ እና እንዲገነዘቡ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
በዚህ ዓመት የሚከበሩት የጳጉሜን ቀናትም የኢትዮጵያ መንሠራራት በሚል መሪ መልዕክት በተለያዩ ኩነቶች መከበራቸውን አንስተዋል።
ጳጉሜን 5 “የነገው ቀን” ዲጂታላይዜሽን የነገዋ ኢትዮጵያ ከፍታ መሠረት እየኾነ መምጣቱን የሚያመላክቱ ተግባራትን በመከወን እና በማሳየት እየተከበረ መኾኑንም ገልጸዋል።
ዛሬ ዲጅታል አማራ 2030 ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዙ ዲጂታል ሲቪል ሠርቪስ፤ ኢትዮ ኮደርስ እና ሌሎች የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶችን በላቀ ደረጃ በማከናወን የክልሉን ሕዝብ ኑሮ ለማሻሻል ቃል የምንገባበት ዕለት ይኾናል ነው ያሉት።
ባለፈው በጀት ዓመት የክልሉ መንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርም ለማሻሻል እና ዲጂታል ሲቪል ሠርቪስ ለመገንባት የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በተሻለ ደረጃ ያከናወንበት ዓመት እንደኾነ አንስተዋል።
የመንግሥት ኢኒሼቲቭ የኾነውን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመተግበር የዜጎች የዘመናት ጥያቄ ኾኖ የቆየውን የአገልግሎት አሠጣጥ ችግር ማሻሻል መቻሉን ተናግረዋል።
በአዲሱ ዓመትም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በማስፋት እና በመተግበር የዜጎችን የመልካም አሥተዳደር ችግር ለመፍታት እና አገልግሎቱን ለማሻሻል በትኩረት እንደሚሠራ አንስተዋል።
የመሪዎችን እና የመንግሥት ሠራተኞችን መረጃ ወደ ሲስተም ለማስገባት በተሠራው ሥራም ከ96 በመቶ በላይ ወደሲስተም እንዲገባ ተደርጓል ብለዋል።
አዲሱ ዓመት በክልሉ የተጀመረውን የአሻጋሪ ዕድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን በአዲስ ተስፋ እና መነሳሳት ለመፈጸም ቃል የምንገባበት እና ለተቋም ግንባታ ከፍተኛ ርብርብ የምናደርግበት መኾን አለበት ነው ያሉት።
አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የደስታ፣ የጤና የፍቅር እና የስኬት እንዲኾንም ተመኝተዋል።
ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
