
በዓል ሲመጣ የገበያ ድምቀት የሚዘነጋ አይደለም። ሁሉም ቤት ያፈራውን አዘጋጅቶ በዓልን ለማሳለፍ በደስታ ስሜት ሲሯሯጥ ይስተዋላል።
ይህንን ተከትሎ ግን በሕገ ወጥ መንገድ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ እና ምርት በመደበቅ ያልተገባ ትርፍ ለማግኘት የሚኳትኑ አካላት አይጠፉም።
ይህንን ችግር ለመከላከል የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ በዓልን ምክንያት በማድረግ በሕገ ወጥ መንገድ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ አካላት ላይ ግብረ-ኀይል አቋቁሞ መረጃን መሠረት ያደረገ እርምጃ እየወሰደ መኾኑን አስታውቋል።
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ አትክልት ሀሳቤ እንደገለጹት የበዓል ገበያ ግብይትን የተረጋጋ ለማድረግ ለሥጋ ቤቶች ጭምር ምርት በጥራት ከማቅረብ ባለፈ ሕገ ወጥ የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ተሠርቷል።
ከሰሞኑ በተለይም በእንቁላል ምርት ላይ የዋጋ ጭማሪ መታዘባቸውን ጠቁመዋል። ችግሩን ለመፍታትም ምርት ከበዛበት ወደ አነስተኛ አቅርቦት ወዳለበት አካባቢ የማጓጓዝ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪዎችን፣ የምርት መደበቅን እና ሕገ ወጥ ደላሎችን ለመቆጣጠር የተቋቋመው ግብረ ኀይል እስከ ፋብሪካዎች ድረስ ክትትል እያደረገ ይገኛል።
በተለይም በባሕር ዳር ከተማ በአምራች ፋብሪካዎች ላይ ጭምር ቁጥጥር እና ክትትል በማድረግ የሥርጭት እና የአቅርቦት ሁኔታዎችን አስቀድሞ የማስተካከል ሥራ መሥራቱን አብራርተዋል።
አምራች ኢንዱስትሪዎችም ምርታቸውን በተገቢው መንገድ እና ዋጋ ለኅብረተሰቡ እንዲያቀርቡ እየተደረገ ነው ብለዋል። በዓልን ምክንያት በማድረግ የሚደረግ የዋጋ ጭማሪን እና የሕገ ወጥ ደላሎችን እንቅስቃሴ ለመከላከል እስከ ቀበሌ ድረስ ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት።
ቁጥጥሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል። የሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራትም አቅርቦትን በማስፋት የበዓል ግብይቱን ለማረጋጋት ጥረት እያደረጉ መኾኑን የገለጹት ምክትል ኀላፊዋ ማኅበረሰቡ እነዚህን አማራጭ የገበያ ማዕከላትን እንዲጠቀምም ጥሪ አቅርበዋል።
በአቋራጭ ለመበልጸግ የሚጥሩ አካላትን ለመከላከል ለሕግ አስከባሪ አካላት ጥቆማ በመስጠት ሕገ ወጥ አሠራሮችን በጋራ መታገል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ማኅበረሰቡ መሰል ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ሲመለከት ጥቆማ በመስጠት ተባባሪ እንዲኾን ጥሪ አቅርበዋል። በሕገ ወጥ ድርጊት ላይ ተሰማርቶ በተገኘ ማንኛውም አካል ላይ የማያወላውል ሕጋዊ እርምጃ የሚወሰድ መኾኑም ተመላክቷል።
ዘጋቢ:- ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
