በቅርቡ ምክረ ሃሳቦችን ለሕዝብ እንደሚያሳውቅ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

9
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በ2018 ዓ.ም የሥራ ዘመን የተሠሩ ዋና ዋና ክንውኖችን እና የቀጣይ ሥራዎችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በ2018 በጀት ዓመት መልካም እና ፈታኝ የሚባሉ ሁነቶች ቢያልፉም ዋናውን የምክክር ጉባኤ አካሂዶ ማጠናቀቁን በስኬት አንስተዋል።
ጉባኤው በጥንቃቄ እና በርካታ ተባባሪ አዘጋጆችን አሳትፎ መከናወኑ እና የምክክርን አዋጭነት በማስገንዘብ የተሠሩ ሥራዎች ለውጤት እንዳበቃውም ገልጸዋል።
ጉባኤው ከሐምሌ 08/2018 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ነሐሴ 16/2018 ዓ.ም መካሄዱን ያነሱት ዋና ኮሚሽነሩ ከ4ሺህ በላይ ተመካካሪዎች ጠንካራ ለውሳኔ የሚጠቅም ምክረ ሀሳቦችን በማዋጣት ኢትዮጵያን ማዕከል አድርገው ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው ተመካክረዋል ነው ያሉት።
ታሪክ ቀያሪ እና ተስፋ ሰጭ የኾነው የምክክር ጉባኤ ሙሉ እንዲኾን የተጀመሩ ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል። ኮሚሽኑ በቀሪ የሥራ ዘመኑ በጉባኤው የቀረቡ ምክረ ሀሳቦችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለሕዝብ ይፋ የማድረግ፣ እንዲተገበሩ የማገዝ፣ ሂደቶችን ግልጽ የማድረግ እና ምክክር በኢትዮጵያ ታሪክ ባሕል እንዲኾን ለማድረግ እንደሚተጋ ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ የነባሩ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከመሰናበታቸው በፊት መስከረም 10/2019 ዓ.ም ምክረ ሀሳቦቹን ለማቅረብ ማቀዱንም ገልጿል።
ለምክክር ጉባኤው ውጤታማነት የተጉ ግለሰቦች ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት የነበራቸውን ውጤታማ አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ለአዲሱ ዓመትም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሞጆ የተገነባውን ዘመናዊ የሎጂስቲክስ ማዕከል ሥራ አስጀመሩ።
Next articleበዓልን ምክንያት በማድረግ ሕገ ወጥ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እየተወሰደ ነው።