ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሞጆ የተገነባውን ዘመናዊ የሎጂስቲክስ ማዕከል ሥራ አስጀመሩ።

8
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሞጆ የተገነባውን ዘመናዊ የሎጂስቲክስ ማዕከል መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ጉዞ በተግባር የታነጸበት ሥራ ብለዋል።
ዛሬ በሞጆ ተገኝተው ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ስኬት ትልቅ ሚና የሚጫወተውን እና በ60 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባውን ዘመናዊ የሎጂስቲክስ ማዕከል ማስፋፍያ የመጀመሪያ ምዕራፍ ማስመረቃቸውን ገልጸዋል።
ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በዓመት እስከ 1 ሚሊዮን ባለ 20 ጫማ ኮንቴነሮች የማስተናገድ አቅም ያላቸው ጣቢያዎችና ዘመናዊ መጋዘኖች አሉት።
የደረቅ ብትን ጭነቶችን በሀገር ውስጥ እንድናሽግ ማስቻሉ፣ የውጭ ምንዛሬን ከመቆጠብ ባለፈ ለዜጎቻችን ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
የማዕከሉን የአሠራር ፍጥነት ለማሳደግ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተተከለው የባቡር ላይ ክሬን ከባቡር መስመር የሚደረገውን የኮንቴነር ዝውውር በከፍተኛ ፍጥነት ያከናውናል ነው ያሉት።
ሙሉ አሠራሩ በዘመናዊ ዲጂታል መሠረተ ልማት የተሳሰረ በመኾኑ ለተገልጋዮች ፈጣን እና አስተማማኝ አገልግሎትን ያሳልጣል። ይህ ማዕከል ከኢትዮ ጅቡቲ መስመር ባሻገር ኢትዮጵያን፣ ደቡብ ሱዳንን እና ዩጋንዳን የሚያስተሳስረው የ‘ደሱ’ ኮሪደር አካል ነው።
ይህም ሀገራችን በዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ ደረጃ ላይ ያላትን ስፍራ የሚያሻሽል እና የቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስራችንን ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ የሚያሸጋግር ትልቅ ድል ነው ብለዋል በመልዕክታቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“የነገው ቀን በዛሬው ብርታታችን፣ ጥረታችን እና መስዋዕትነታችን የሚመሠረት ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleበቅርቡ ምክረ ሃሳቦችን ለሕዝብ እንደሚያሳውቅ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።