“የነገው ቀን በዛሬው ብርታታችን፣ ጥረታችን እና መስዋዕትነታችን የሚመሠረት ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

10
ጳጉሜን 5 የነገው ቀን በአማራ ክልል በተለያዩ ኹነቶች እየተከበረ ነው። ቀኑን የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ፣ የአማራ ክልል ሥራ እና ክህሎት ቢሮ፣ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ፣ የአማራ ክልል የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ እና የአማራ ክልል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ናቸው በጋራ ያዘጋጁት።
በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የነገው ቀን በዛሬው ብርታታችን፣ ጥረታችን እና መስዋዕትነታችን የሚመሠረት ነው ብለዋል።
ዛሬ ላይ የተረጋጋ ተቋም የገነባ ነገ የተረጋጋ ሀገር እና ማኅበረሰብ ይገነባል ነው ያሉት። ዛሬ ላይ የሠራ ነገ የበለጸገ ማኅበረሰብ መፍጠር እንደሚችልም ገልጸዋል።
ዛሬ በሰው ኀይል፣ በኢኮኖሚ እና በቴክኖሎጂ የሠራ የነገውን ብልጽግና እንደሚቆጣጠር ተናግረዋል። ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት ያደረገ ሀገር ነገውን እንደሚያሳምርም ነው የገለጹት።
ዛሬ ያሉትን ችግሮች እየፈታን ለነገው መዳረሻችን መዘጋጀት ይጠበቅብናል ነው ያሉት። ዛሬን ሠርተን ነገን የተሻለ ማድረግ አለብንም ብለዋል።
የአማራ ክልል መንግሥት ነገውን በማሰብ የአሻጋሪ ዕድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ በማቀድ እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
መሪ መልዕክታችን አርቆ ማየት አልቆ መሥራት ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ዛሬ ላይ አልቀን በመሥራት እና አርቆ በማየት ነገን መቆጣጠር አለብን ብለዋል።
የነገ ዋስትናችን ዛሬ ነው፤ ነገን ዝም ብለን ማማተር የለብንም፤ ዛሬን ነው መሥራት ያለብን ነው ያሉት። ነገን ለማሳመር ደግሞ ቴክኖሎጂ ላይ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ለቴክኖሎጂ የተመቸ ተቋም እና ማኅበረሰብ መገንባት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 አካል የኾነው ዲጂታል አማራ፣ ዲጂታል ሲቪል ሰርቪስ እና ኢትዮ ኮደርስ ነገን ለማሳመር የተጀመሩ ሥራዎች መኾናቸውን ገልጸዋል። ነገን ለማሳመር ዛሬ ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የነገው ቀን አዲሱ ዓመት ለሁሉም ብሩህ እንዲኾን ተመኝተዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleትምህርትን መደገፍ ሀገር አሻጋሪ ትውልድን መፍጠር ነው።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሞጆ የተገነባውን ዘመናዊ የሎጂስቲክስ ማዕከል ሥራ አስጀመሩ።