
ሁለንተናዊ የካዳስተር ሥርዓትን ለማጠናከር እና የመሬት መረጃን በዲጂታል መንገድ ለማሥተዳደር የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር ጋር ለመሥራት ተስማምተዋል።
በከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የመሬት እና ካዳስተር መሪ ሥራ አሥፈጻሚ ብዙዓለም አድማሱ እንደገለጹት የመሬት አሥተዳደርን በካዳስተር ሥርዓት ማዘመን የዜጎችን የንብረት መብት ከማስጠበቅ ባለፈ የከተሞችን የውስጥ ገቢ ለማሳደግ እና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ሥርዓቱ ሕጋዊ ካዳስተርን፣ ፊዚካል ካዳስተርን እና ሁለንተናዊ ካዳስተርን በማቀናጀት የመሬት መረጃን በተደራጀ መንገድ ለማሥተዳደር ያግዛል ተብሏል።
የአገልግሎቱ ዲጂታል መኾን የአገልግሎቱን ቅልጥፍና ከማሻሻል ባለፈ ሙስናን ለመከላከል እና የዜጎችን የንብረት መብት ለማስጠበቅ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ መኾኑ ተጠቁሟል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት የመሬት መረጃዎች በአስተማማኝ እና በተጠበቀ ሁኔታ እንዲስተናገዱ የራሱን ወሳኝ ሚና እንደሚጫወትም አረጋግጧል።
የስምምነቱ ዋና ዓላማም የተጠበቀ የዲጂታል አገልግሎት ማቅረብ፣ የመረጃ ቅንጅት እና መስተጋብርን ማጠናከር፣ የኢ-ላንድ እና ሌሎች ዲጂታል አገልግሎቶችን ማሳደግ፣ የሳይበር ደኅንነትን ማረጋገጥ እንዲሁም የ”2D” እና “3D” የካዳስተር አገልግሎቶችን ማዘመን ነው።
የጂኦስፓሻል እና ስማርት ክፍያ ዳይሬክተር ቢኒያም አበባው የመሬት መረጃ ወሳኝ ሀገራዊ ጉዳይ በመኾኑ ተቋማቱ በጋራ መሥራታቸው ወቅታዊ እና አስፈላጊ መኾኑን አንስተዋል።
ሁለቱ ተቋማት ሁለንተናዊ የካዳስተር ሥርዓትን በማጠናከር የመሬት መረጃ አያያዝን ለማዘመን፣ የዜጎችን የንብረት መብት ለማስጠበቅ እና የዲጂታል አገልግሎቶችን ለማሳደግ በጋራ ለመሥራት ተፈራርመዋል።
ዘጋቢ፦ አየለ መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
