
እርሷ በጽኑዎች የተጠበቀች፤ በጽናት የኖረች፤ ለጠላት ያልተበገረች፤ ታሪኳን ሁሉ በድል የጻፈች፤ የተነሱባትን ሁሉ ያንበረከከች የጽኑዎች ሀገር ናት።
አርሷ ፈተና አይበግራትም፤ መከራ አያስቆማትም፤ የጦር ፍላጻ አያስደነግጣትም፤ የጠላቶች መብዛት አያሸብራትም ሁሉንም በጽናት ታልፈዋለች፤ በጀግንነት ድል ታደርጋቸዋለች፤ በልጆቿ አንድነት ትሻገረዋለች እንጂ።
እርሷ የጀግና ምድር ናት ጀግኖች የሚፈጠሩባት፤ በጀግንነት የሚጠብቋት፤ ጠላቶቿን የሚቀጡላት፤ ክብሯን እና ስሟን ከፍ ከፍ የሚያደርጉላት፤ እርሷ የነጻነት ምድር ናት ቅኝ ገዢ ሁሉ እጅ የሰጠባት፣ እየተሸነፈ የተመለሰባት፤ እርሷ የነጻነት ብርሃን ናት በቅኝ ግዛት ጨለማ የነበረ ሁሉ ብርሃን ያየባት፤ ከጨለማ የወጣባት፤ የነጻነት መንገድን ለማግኘት ብርሃን ያገኘባት፡፡
እርሷ የአንድነት ምድር ናት በአንድነት የተጠበቀች፤ በልጆቿ አንድነት ነጻነቷን ያጸናች፤ ሉዓላዊነቷን ያስከበረች፣ ከራሷ አልፋ ለጥቁር ዘር ሁሉ አርአያ የኾነች፣ የነጻነት እናት የተባለች፡፡
እርሷ የማትደፈር ናት ብርቱ ልጆች ያሏት፣ ፈተናዎችን ሁሉ የሚያሻግሯት፤ ጠላቶቿን ሁሉ የሚቀጡላት።
ኢትዮጵያ ከፈተና በላይ የኾነች፣ ከጠላቶቿ ሁሉ የላቀች እና በታሪኳ ለየትኛውም ጠላት ያልተንበረከከች ሀገር ናት፡፡ በየዘመናቱ አያሌ ጠላቶች ተነስተውባታል ነገር ግን ሁሉንም ድል ያደረገች አስደናቂ ሀገር ናት፡፡ ዛሬም እንደ ትናንቱ ብዙ ጠላቶች አሉባት፡፡ ነገር ግን በልጆቿ ብርታት፣ ጽናት እና አንድነት ሁሉንም ድል ትመታቸዋለች፡፡ እንደ ትናንቱም በአሸናፊነት ትገሰግሳለች።
ጳውሎስ ኞኞ የኢትዮጵያ እና የጣሊያን ጦርነት በተሰኘው መጽሐፋቸው ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ለሺህ ዓመታት ያህል የተደጋገመ ሙከራ ተደርጓል። ኢትዮጵያውያን ግን ሀገራቸውን በሌላ ባዕድ ሳያሲዙ ባላቸው ኀይል ሲከላከሉ ቆይተዋል ይላሉ።
በአውሮፓም ኾነ በኤሲያ ወይም በአፍሪካ የሚነሱ ታላላቅ መንግሥታት ጉልበት እያገኙ ግዛታቸውን በሚያሰፉበት ጊዜ ኢትዮጵያንም ለመደረብ ብዙ ጊዜ ሞክረዋል። ኢትዮጵያውያን ግን ለማንም ሳይበገሩ እና ሳይገብሩ እስከአሁን ሀገራችንን አስከብረው ቆይተዋል ብለው ጽፈዋል።
ኢትዮጵያን አስገብሮ ለመያዝ የተደጋገመ የውጭ ጦር ቢመጣም ኢትዮጵያውያን ባላቸው ኀይል የማይበገሩ ኾነው የሚመጣውን የውጭ ጦር ሁሉ መልሰዋል። ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን የማይለቁ እና የሌላ ሀገር የማይፈልጉ ኾነው እንጂ ሌሎችንም የሚይዙበት አቅም እና ዘመን ነበራቸው ይላሉ።
የጦር ኀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ለኢትዮጵያ ክብር እና ሉዓላዊነት የተዋደቁ
አያቶቻችን ከሰማይ የመርዝ ዝናብ እየዘነበባቸው በጎራዴ እና በዲሞፍተር ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ሥር ሳይጥሉ አንድነቷን ጠብቀው አስረክበውናል ነው የሚሉት፡፡
ዛሬ የቴክኖሎጂ ግኝቶችን የታጠቅንበት፣ የሰው ኪሣራ ቀንሰን በነበልባል አቅም የምንዋጋበት አቅም ላይ እንገኛለን፤ ዘመናዊ መሣሪያ ሳይታጠቁ ሀገር ያስረከቡን አያቶቻችን አጥንት እንዳይወጋን ባገኘነው ዕድል ተጠቅመን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር መታገል አለብን ነው የሚሉት፡፡
ታሪካዊ እና ወቅታዊ ጠላቶቻችን ኢትዮጵያን ከምሥራቅ አፍሪካ ካርታ ላይ ለማጥፋት ቢሞክሩም አልቻሉም፤ በዚህ ዘመን ለመምጣት ቢሞክሩም ኢትዮጵያን አይችሏትም፤ ነገር ግን በባንዳዎች አማካኝነት ኢትዮጵያን እየሞከሯት ነው፣ ሥደተኛ እና ሰርጎ ገብ ባንዳ የራሱን ሀገር አደጋ ላይ ለመጣል እየሠራ ነው ብለዋል፡፡
መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያ ምሽግ እና መከታ ነው፤ ሠራዊቱ ሀገር ለማፍረስ የሚተጉ ጽንፈኞችን እና ነውጠኞችን እየመከተ ነው ይላሉ።
ከሁሉም በፊት ሀገር ይቀድማል፤ ሥልጣንም ኾነ ፖለቲካ ከሀገር ሕልውና ጋር የማይገዳደር መኾን ይገባዋል ነው ያሉት፡፡ ሀገራችንን እናፈርሳለን የሚሉትን እንመክታለን፣ ሀገር እናጸናለን፣ ለልጆቻችንም እናስተላልፋለን ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያን ልጆቿ በጽናት ይጠብቋታል፤ አስከብረውም ያኖሯታል፤ ጠላቶቿንም ይቀጡላታል። በድል አድራጊነትም ያራምዷታል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
