የበጎነት እና የጽናት ምሣሌው ቢኒያም በለጠ!

17
በዓለማችን ላይ ጥቂት ሰዎች ብቻ የራሳቸውን ደስታ፣ ምቾት፣ ክብር፣ እና ጥቅም ወደ ጎን በመተው ለሌሎች ሕይወት ይኖራሉ። ሙሉ ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን እና ጉልበታቸውን ሰውተው ለሌሎች መኖርን ይመርጣሉ።
ከእነዚህ ጥቂት አብሪ ከዋክብት እና የሰብዓዊነት ተምሳሌቶች መካከል የክብር ዶክተሩ ቢኒያም በለጠ አንዱ ናቸው።
ቢኒያም የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት ተምረዋል፡፡ በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና አራት ነጥብ አምጥተዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሕግ እንደተመረቁም በአንድ ወቅት ከሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል። ዓቃቤ ሕግ በመኾንም ለ3 ዓመታት በሙያቸው አገልግለዋል። ወደ አሜሪካ በማቅናት የሁለተኛ ዲግሪያቸውንም ይዘዋል። ለ7 ዓመታት ያህል በአሜሪካ በሥራ አሳልፈዋል።
ከአሜሪካ ተመልሰው ከልጅነታቸው ጀምሮ ሲያልሙት የነበረውን የበጎ አድራጎት ሥራ በ2002 ዓ.ም በቤተሰቦቻቸው መኖሪያ ቤት ነበር የጀመሩት። ቀጥለውም 40 የሚኾኑ ኤጋውያንን በመያዝ መቄዶንያ የአረጋውያን እና የአዕምሮ ሕሙማን ማዕከልን በ2004 ዓ.ም መሠረቱ።
“ሰው ለመርዳት ሰው መኾን በቂ ነው” በሚል ቅን ልቦና በትንሹ የመሠረቱት የአዕምሮ ሕሙማን ማዕከል ዛሬ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ አገልግሎት የሚሰጥ ግዙፍ ተቋም ኾኗል። በአሁኑ ወቅት ከ8 ሺህ በላይ አረጋውያንን እና የአዕምሮ ሕሙማንን በማዕከሉ አሰባስበው የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በጽናት አስቀጥለዋል። ማዕከሉ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በበርካታ ከተሞችም በመስፋት ላይ ይገኛል።
ማዕከሉ በርካታ ወጣቶች በበጎ ፈቃደኝነት እና በቋሚነት በሰብዓዊ አገልግሎት ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ የተስፋ እና የፍቅር ዘር ዘርተዋል።
በርካታ መሰናክሎችን አልፈው ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ የበቁት በሥራቸው እና በተግባራቸው ባሳዩት ጽናት ነው። ለዚህ በጎ አበርክቷቸው የበጎ ሰው ሽልማት፤ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የክብር ዶክትሬት ተበርክቶላቸዋል።
“በጎነትን ከአባቴ ተምሬዋለሁ” የሚሉት ባለታሪኩ ማስተዋል፣ ስክነት እና ለሰው መኖርን ከወላጆቻቸው የወረሱት ባህርይ ስለመኾኑም ይናገራሉ። ሲበዛ ዝምተኛ ናቸው። ፈጣሪያቸውን አብዝተው ያመሠግናሉ።
​የቅንጦት ሕይወታቸውን ትተው፣ ክብርን በሰብዓዊነት ቀይረው የብዙዎችን ሕይወት ታድገዋል። ከመንገድ ወድቀው የነበሩትን የሀገር ባለውለታዎችን አንስተዋል። የተስፋ መቁረጥን ጨለማ በበጎነት ብርሃን ለውጠዋል።
ሁሌም ገና ምንም እንዳልሠሩ ደጋግመው ይገልጻሉ። ራሳቸውን በትሕትና ጥላ ስር ዝቅ አድርገው ይናገራሉ። ሥራቸው ግን ከፍ ብሎ ጎልቶ ይታያል። ከአንደበታቸው ይልቅ ተግባራቸው ቀድሞ ይገለጣል።
በቢኒያም መኖር በሺዎች የሚቆጠሩ አቅመ ደካሞች እና አረጋውያን እንባቸው ታብሷል፤ ተስፋቸው ለምልሟል፤ ሕመማቸው ተፈውሷል። ብዙዎች ወደ ውጭ ሀገር ተጉዘው የተሻለ ሕይወት ለመኖር በሚመኙበት እርሳቸው ግን የራሳቸውን ምቾት ሰውተው የብዙዎችን ሕይወት እየታደጉ በጽናት ቀጥለዋል። ጽናትን በተግባር አሳይተው የዘመናችን የሰብዓዊነት ምልክት መኾን ችለዋል።
ይህ በጎ ተግባራቸው ለሰብዓዊነት ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር እና ጽናት የሚያሳይ በመኾኑ የጽናት ተምሳሌትነት ኾነው በዛሬው የጽናት ቀን ልናስታውሳቸው ወደድን።
✍️በአሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየዓባይ ጀግኖች ዕውቅና ተሰጣቸው።
Next article‎”ጽናትን ከትጋት፣ ትጋትን ከውጤታማነት፣ ውጤታማነትንም ከዘላቂ ብልጽግና ጋር ማቀናጀት ይገባል” አቶ ይርጋ ሲሳይ