
ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ኢትዮጵያውያን እና ባለድርሻ አካላት የምሥጋና እና የዕውቅና መርሐ ግብር ተካሂዷል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ባለፉት 14 ዓመታት ከውስጥ እና ከውጭ የተጋረጡትን በርካታ ፈተናዎች ተቋቁሞ ለፍጻሜ መድረሱ የመንግሥት እና የሕዝብ የጋራ ርብርብ ውጤት መኾኑን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አረጋዊ በርሄ (ዶ.ር) ገልጸዋል።
ዶክተር አረጋዊ በርሄ የግድቡ ግንባታ የአንድ ተቋም ወይም የአንድ ወገን ሥራ ሳይኾን፣ የመላው ሕዝብ ተሳትፎ እና የመንግሥት ርብርብ የተጣመረበት የጋራ ውጤት ነው። ሕዝቡ በግድቡ ግንባታ ያሳየው የሞራል፣ የፋይናንስ እና የተለያዩ ድጋፎች ፕሮጀክቱ በፈተናዎች ውስጥ እስከ ፍጻሜ እንዲደርስ ያስቻሉ መኾኑን አመልክተዋል።
የሕዝብ ተሳትፎ በሕዳሴ ግድብ ብቻ የሚያበቃ ሳይኾን በቀጣይ የሀገር ግንባታ እና የልማት ሥራዎች መጠናከር እንዳለበትም ጠቁመዋል።
የሀገር ግንባታ በመንግሥት ብቻ የሚሳካ ሳይኾን፣ የኅብረተሰቡን ንቁ ተሳትፎ፣ ትጋት እና ኀላፊነት የሚጠይቅ በመኾኑ የሕዳሴ ግድብ ተሞክሮ በሌሎች የልማት ዘርፎችም ሊደገም እንደሚገባ ኀላፊው አስገንዝበዋል።
የግድቡ ጉዞ እና የሕዝብ ተሳትፎ ታሪክ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ፣ “የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የጽናት ተምሳሌት” የተሰኘ መጽሐፍ መዘጋጀቱንም ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል።
በመርሐ ግብሩ መጨረሻም በግድቡ ጉዞ ውስጥ ላቅ ያለ አበርክቶ ለነበራቸው ኢትዮጵያውያን እና ባለድርሻ አካላት ምሥጋና እና ዕውቅና ተሰጥቷል። ዶክተር አረጋዊ በርሄም በግድቡ ጉዞ ጠንካራ ተሳትፎ እና ድጋፍ ላደረገው መላው ሕዝብ ምሥጋና አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
