
ለአዲስ ዓመት የኃይል መቆራረጥ እንዳይኖር ሰፊ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል።
2 ሺህ 110 ኪሎ ሜትር የኃይል መስመር እና ከ8 ሺህ በላይ ትራንስፎርመሮች መፈተሻቸውንም ተቋሙ ገልጿል።
በበዓሉ ዋዜማ እና በበዓሉ ዕለት ሊከሰቱ የሚችሉ የኃይል መቆራረጦችን በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የተቋሙ መዋቅሮች ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በቅንጅት የተደራጀ ሥራ እያከናወኑም ይገኛሉ። 24 ሰዓት ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ የቴክኒክ ቡድን ተዘጋጅቷልም ተብሏል።
በተጨማሪም በሁሉም የአገልግሎቱ ሪጅኖች እና የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት አጣዳፊ የጥገና ሥራዎችን ለማከናወን ዝግጁ የጥገና ቡድኖች መደራጀታቸውን ከአገልግሎቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ሰፊ የኔትዎርክ ፍተሻ እና የጥገና ሥራ እንደተከናወነም ተገልጿል።
በነሐሴ ወር በመላ ሀገሪቱ እና በአዲስ አበባ በተከናወኑ ሰፊ የፍተሻ እና የጥገና ሥራዎች 2 ሺህ 110 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር እንደተፈተሸም መረጃው ያመላክታል። በፍተሻው የተለዩ 10 ሺህ 308 የኃይል መቆራረጥ ሊያስከትሉ የሚችሉ ግኝቶችም ሙሉ በሙሉ ተስተካክለዋል ተብሏል።
ከ8 ሺህ በላይ ትራንስፎርመሮች የተፈተሹ ሲኾን በ6 ሺህ 877 ትራንስፎርመሮች ላይ የተለያዩ የቴክኒክ ችግሮች እንዲስተካከሉ መደረጉም ተመላክቷል።
ለደንበኞች የኃይል ቆጣቢነት እና ጥንቃቄ ጥሪ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ ቢያጠናቅቅም እንኳ በበዓሉ ወቅት የሚፈጠረውን ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት እና ጭነት ለማመጣጠን ደንበኞች ኃይል ቆጣቢ ቁሳቁሶችን እንዲጠቀሙ እና የኤሌክትሪክ ቁሳቁሶቻቸው ለአደጋ የማያጋልጡ መኾናቸውን እንዲያረጋግጡም ጥሪ ቀርቧል።
የኃይል ጭነት በማይበዛበት ሰዓት በተለይም ከምሽቱ 4፡00 እስከ ንጋቱ 11፡00 ባለው ጊዜ የኤሌክትሪክ ቁሳቁሶችን መጠቀም የተሻለ አማራጭ መኾኑንም መረጃው ይጠቁማል።
ደንበኞች በበዓሉ ወቅት ድንገተኛ የኤሌክትሪክ አደጋ ሲያጋጥማቸው ወይም የጥገና ጥቆማ እና አስተያየት ለመስጠት 905 በመደወል በነጻ ማሳወቅ ይችላሉም ይላል መረጃው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
