
በደቡብ ወሎ ዞን በመንግሥት እና በማኅበረሰብ ተሳትፎ ለሚገነባው የአንቻሮ ሁለገብ ጤና ኬላ ግንባታ የማስጀመሪያ መርሐግብር ተካሂዷል። በመርሐግብሩ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) አንቻሮ ቀደምት እና ጥንታዊ ከተማ፤ የንግድ እና የባሕል ማዕከል መኾኗን ጠቅሰዋል።
የጤና ኬላው ግንባታ ጤናው የተጠበቀ ኅብረተሰብ ለማፍራት ለሚደረገው ጥረት አጋዥ መኾኑን አመላክተዋል።
ለአንቻሮ ጤና ጣቢያ ግንባታ የወሎ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የአካባቢው ተወላጆች እና ባለሃብቶች እያደረጉት ላለው አስተዋጽኦ አመሥግነዋል።
የክልሉ መንግሥትም የጤና አገልግሎቱን የተሳለጠ ለማድረግ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።
ከተማዋ ወደ ጥንታዊ ከፍታዋ እንድትመለስ ለማድረግም በትብብር መሥራት እንደሚገባም ጠቅሰዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን ከመንግሥት አቅም ባሻገር በማኅበረሰቡ እና በባለሃብቶች የተጀመረው እንቅስቃሴ የሚደነቅ መኾኑን ገልጸዋል።
የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል እየሠራን እንገኛለን ያሉት አሥተዳዳሪው የጤና ጣቢያው ግንባታ እንዲጠናቀቅ የዞኑ አሥተዳደር አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል። ባለሃብቶች እያደረጉት ላለው ድጋፍም አመሥግነዋል።
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉ ባለሃብቶች እና የአካባቢው ተወላጆችም ጥንታዊቷን አንቻሮ ወደ ቀደምት ከፍታዋ ለመመለስ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድጋፍ እያደረጉ መኾናቸውን አንስተዋል።
ዘጋቢ:- ተመስገን አሠፋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
