
ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ በልጃገረዶች እና በታዳጊ ወጣቶች ጥበባዊ ክዋኔዎች ታጅቦ ሲከበር የቆየው የአዲስ ዓመት ማብሰሪያው የአሱሪቴ በዓል ማጠቃለያ መርሐ ግብር በእንጅባራ ከተማ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
በማጠቃሊያ መርሐ ግብሩ በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከሁሉም ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች የተውጣጡ የባሕል ቡድን ልዑካን እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል። በበዓሉ በጎዳና ላይ የባሕል ጭፈራዎች እና ባሕሉን የሚያንጸባርቁ ልዩ ልዩ ትዕይንቶችም ቀርበዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ቃለአብ ከሃሊ ሰላም የሚሰበክበት፤ ለአዲስ ዓመት ተስፋ የሚደረግበት እና የጎላ ማኅበራዊ መስተጋብር የሚንጸባረቅበት ይህ በዓል ባሕላዊ እሴቱን ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ክንዴ ብርሃን (ዶ.ር) አሱሪቴ በአገው ማኅበረሰብ ዘንድ ለረጅም ዓመታት ሲከወን የቆየ ጥልቅ ባሕላዊ እና ማኅበራዊ ፋይዳ ያለው ተወዳጅ ባሕል መኾኑን ገልጸዋል። በተለያዩ ምክንያቶች ደብዝዞ መቆየቱንም ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲው ከብሔረሰብ አሥተዳደሩ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ጋር በመተባበር በሠራቸው ተግባራት በ2017 ዓ.ም ባሕሉ ወደ አደባባይ እንዲመለስ ተደርጓል ነው ያሉት።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ አይተነው ታዴ አሱሪቴ ጥላቻ በፍቅር የሚሸነፍበት፤ የእርቅ እና የመተሳሰብ እሴቶች ጎልተው የሚታዩበት መተሳሰሪያ ገመድ መኾኑን ተናግረዋል። ባሕሉ ለተተኪው ትውልድ እንዲተላለፍ መጠበቅ እና መንከባከብ ከሁሉም ይጠበቃልም ነው ያሉት። የበዓሉ ታዳሚዎችም አሱሪቴ እርስ በርስ የሚተዋወቁበት የፍቅር እና የአንድነት በዓል መኾኑን ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
