ለአማራ ሕዝብ የማይናወጥ ማንነቱ ጽናቱ ነው።

11
የአማራ ክልል የጸጥታ ተቋማት “ጽኑ መሠረት ለማንሰራራት” በሚል መሪ መልዕክት የጽናት ቀንን በተለያዩ ዝግጅቶች አክብረዋል። የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ፣ የሚሊሻ ኮሚሽን፣ የማረሚያ ቤት ኮሚሽን እና የፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጸጥታ አባላት እና ሠራተኞች በመድረኩ ታድመዋል።
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) ክልሉን እና ሕዝቡን ለመበተን እንዲሁም መንግሥትን ለማፍረስ የተወጠነው አፍራሽ ሴራ በሕዝቡ እና በጸጥታ ኀይሉ ጥንካሬ፣ አንድነት እና ጽናት መክሸፉን ገልጸዋል። በነበሩት ፈተናዎች ውስጥም ታላላቅ መድረኮች (እንደ ጣና ፎረም ያሉት) ሳይቋረጡ መከናወናቸውን አንስተዋል።
የፖሊስ ሠራዊት እና የማረሚያ ቤት ተቋማት ራሳቸውን በማጠናከር ሰላም በማስፈን ረገድ የጎላ ሚና እየተጫወቱ መኾኑንም ገልጸዋል። በቀጣይም የሚታዩ አፍራሽ እንቅስቃሴዎችን በጽናት በመታገል እና በማረም ጠንካራ እና ሰላማዊ ክልል ለመገንባት በጋራ እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ጥጋቡ ይልማ ጽናት እና መስዋዕትነት ሕይወትን፣ ጊዜን እና አካልን ለሕዝብ፣ ለሀገር ጥቅም እና ለሕገ-መንግሥት አሳልፎ መስጠት ነው ብለዋል። ይህ መስዋዕትነት ትርጉም የሚኖረው ከግል ፍላጎት የጸዳ እና ከትልቅ ሀገራዊ ዓላማ ጋር ሲቆራኝ ብቻ ነውም ብለዋል።
ታሪክ በሰው ልጆች ጥረት እና ተግባር የሚሠራ መኾኑን በመጠቆም አሁን የሚሠራው ሥራ ሁሉ ነገ ታሪክ ኾኖ ስለሚመዘገብ እያንዳንዱ አካል የራሱን ታሪካዊ አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) ጽናት የአማራ ሕዝብ የማይናወጥ ማንነቱ ነው ብለዋል። ሕዝቡ በተለያዩ ጊዜያት የገጠሙትን ልዩ ልዩ ፈተናዎች በአንድነት እና በባሕላዊ እሴቱ ማለፍ መቻሉንም ተናግረዋል።
የጽናት ቀን የሀገርን ሉዓላዊነት እና የሕዝብን ደኅንነት ላስጠበቁ ጀግኖች ዕውቅና የሚሰጥበት ነውም ብለዋል።
ሕዝቡ ከውጭ እና ከውስጥ ጽንፈኛ ኀይሎች የገጠሙትን ፈተናዎች ተቋቁሞ ፀንቶ መቆም በመቻሉ አሁን ላይ በክልሉ ከፍተኛ የሰላም መሻሻል መምጣቱን ተናግረዋል።
ለዚህ የሰላም መሻሻል ደግሞ የፌዴራል እና የክልሉ የጸጥታ ተቋማትን ጨምሮ የኅብረተሰቡ (የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች እና ምሁራን) ቅንጅታዊ ጥረት ወሳኝ እንደነበር ገልጸዋል።
ክልሉን ወደ ቀደመ ሰላሙ እና ልማቱ ለመመለስ ልዩነቶችን በውይይት እና በመቻቻል መፍታት እንደሚገባም ጠቁመዋል። ያጋጠሙ ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ጠንካራ ኢኮኖሚ ያላት፣ የሕግ የበላይነት የሰፈነባት እና ሰላማዊ ኢትዮጵያን ለመገንባት በአንድነት መነሳት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleበአዲሱ ዓመት የጦርነት አባዜ ያክትም፤ የሰላም ብርሃን ይንጋ!
Next article“በጽናት የተመዘገቡ ድሎቻችንን ማስቀጠል ይገባል” ርእሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ