በአዲሱ ዓመት የጦርነት አባዜ ያክትም፤ የሰላም ብርሃን ይንጋ!

10
ሦስት ዓመታት ለአንዳንዶች አጭር ጊዜ ሊመስል ይችል ይኾናል፤ ሰላም ለራቀባቸው ሕዝቦች ግን እያንዳንዱ ቀን በስጋት፣ በእንባ እና በጭንቀት የተሞላ የሰቀቀን ዓመታት ኾኖ ነው እያለፈ ያለው። የትናንቱ የሰላም አየር በባሩድ ጭስ ታፍኖ፣ ሕይወት ከማሳደድ እና ከመሸሽ ጋር ተቆራኝቷል። እንደ ልብ ተንቀሳቅሶ መሥራት፣ አምርቶ መሸጥ፣ ገዝቶ መብላት እና ዘመድ ወዳጅን መጠየቅ የቅንጦት ኾኖ ከራርሟል።
በትጥቅ ትግል ውስጥ የነበሩ እና የሰላምን አማራጭ የተቀበሉ ወገኖች ጦርነቱ ማኅበረሰቡን ከራሱ ቀዬ ከማፈናቀሉም በላይ የፈጠረው ሰብዓዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ ፈታኝ መኾኑን በተደጋጋሚ ሲመሰክሩ ታይተዋል።
በመሠረታዊ የሕክምና አቅርቦት እጦት እና የአምቡላንስ አገልግሎት በመቋረጡ ብቻ እናቶች በወሊድ ምክንያት ለህልፈት ሲዳረጉ መቆየታቸውም የሰላምን መንገድ እንዲከተሉ አድርጓቸዋል። እገታ እና ዝርፊያውም የዕለት ከዕለት ክስተት ኾኖ ማኅበረሰቡ በገዛ ቀዬው ባይተዋር እንዲኾን መፍረድ የለብንም በሚል ለሕዝብ ጥያቄ የክብር ምላሽ ሰላምን ምርጫ አድርገዋል። ልብን ክፉኛ የሚሰብረው ግን የነገው ትውልድ እጣ ፈንታ ነው።
በ2015 ዓ.ም ክረምት ላይ በጉጉት የተገዙ ደብተሮች ቀለም ናፍቋቸዋል። ቦርሳዎች ደብተርና መጽሐፍትን ናፍቀው ባዶ ከርመዋል። እስክርቢቶዎችም ሳይጽፉ ቀለማቸው ደርቋል። በአንዳንድ አካባቢዎች የልጆች የመማር ተስፋ፣ የወደፊት ሕልም እና ሀገር ተረካቢነታቸው በታጣቂዎች የውሳኔ ሀሳብ ላይ ተንጠልጥሎ ቀርቷል።
የሕዝቡ የሰላም ጥማት ግን ዛሬም በዝምታ ውስጥ ይጮኻል። አሁን “ግጭት ከሦስት ዓመት በላይ በቂ ነው!” የሚለው ድምጽ ከየአቅጣጫው እየተሰማ ነው። እናቶች በእንባ፣ አባቶች በጸሎት፣ ወጣቶች በምኞት ሰላምን እየጠሩ ነው።
የቀድሞ ታጣቂ የነበሩት ኢያሱ አባተ ጦርነት ሀገርን ከማዳከም እና ትውልድን ከማስጨረስ ውጭ ትርፍ እንደሌለው ተናግረዋል። ሕዝቡም ጳጉሜን የሰላም ቀን አድርጎ በየዓመቱ ለማሰብ የታጠቁ ወገኖች በቀሪ ቀናት የሰላምን አማራጭ ተቀብለው ለአዲስ ዓመት የሰላም ብስራት እንዲያሰሙ እየተማጸነ ነው። ከሰሞኑ በርካታ ታጣቂዎች ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ በመስጠት ላይም ናቸው።
አዲሱ የ2019 ዓ.ም የመሳሪያ ድምጽ የማይሰማበት፣ ልጆች ወደ ትምህርት ገበታቸው የሚመለሱበት፣ አርሶ አደሮች ወደ ማሳው የሚወጡበት እና እናቶች ያለ ስጋት ወልደው የሚስሙበት ዓመት እንዲኾን የሁሉም ምኞት ነው። በመኾኑም የታጠቁ ወገኖች የሕዝቡን እንባ በማበስ እና የልጆችን ተስፋ በመመለስ ለሀገር የሚበጀውን ሰላም እንዲመርጡ የመላው ሕዝብ ፍላጎት ነው።
የሚያዋጣው ሰላማዊ ትግል ነው በሚል የሕዝብ እና የመንግሥትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉት ኢያሱ አባተ የጋራ መግባባት እና ሰላም ሁሉም ወገን አሸናፊ የሚኾንበት ብቸኛ መንገድ ነው ብለዋል። እያንዳንዱ ዜጋም የተጀመረውን የሰላም ጥረት በመደገፍ ሀገርን ወደ መደበኛ ሕይወት ለመመለስ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleኢትዮጵያ የሉዓላዊነት አደጋዎችን በልጆቿ ጀግንነት እያከሸፈች ለዘመናት የጸናች የአፍሪካ የነፃነት አርማ ናት።
Next articleለአማራ ሕዝብ የማይናወጥ ማንነቱ ጽናቱ ነው።