
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጳጉሜን 3 የጽናት ቀንን የከተማው የሥራ ኀላፊዎች፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የፌዴራል ፖሊስ አባላት፣ የሰላም አስከባሪዎች፣ የሚሊሻ አባላት እንዲሁም ነዋሪዎች በተገኙበት በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል።
በዕለቱ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው
ኢትዮጵያ በውስጥ እና በውጭ ኀይሎች የሚሰነዘሩባትን የሉዓላዊነት አደጋዎች በልጆቿ ጀግንነት እና በአይበገሬነት በማክሸፍ ለዘመናት የጸናች የአፍሪካ የነፃነት አርማ መኾኗን ገልጸዋል። ክብሯን አስጠብቃ የኖረች የነፃናት ተምሳሌት ሀገር ናትም ብለዋል። በልጆቿ ደም እና አጥንት ጸንታ የቆመች ሀገር ናትም ነው ያሉት።
ጽናት የአባቶቻችን እና የእናቶቻችን አርበኝነት እና የጀግንነት ታሪክ ነው። ጠላቶች ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ቢሞክሩም እንደ አለት የጸናች በመኾኗ አልቻሉም ነው ያሉት። የጽናት ቀንን ስናከብር የተረከብነውን ታሪክ ለነገ በማስተላለፍ ነው ብለዋል። የሚሰነዘሩ ሴራዎችን ማክሸፍ እና ነፃነቷን ማስጠበቅ ይገባልም ነው ያሉት። ጽናትን በትውልድ ቅብብሎሽ ማስቀጠል ዛሬም እንደ ትናንቱ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
” ያለንበትን የፈተና ወቅት በጽናት ለመሻገር አንድነትን ማጠናከር ይገባል” ነው ያሉት። የጸጥታ ኀይሉ የሀገርን እና የሕዝብን ሰላም ለማረጋገጥ እያደረገ ያለውን የማይበገር ተጋድሎ ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ነው የገለጹት። ከተማዋን የሰላም፣ የኢኮኖሚ ማዕከል እና ዓለም አቀፍ መዳረሻ ለማድረግ የተጀመረው የልማት ጉዞ በምንም መልኩ የማይቆም መኾኑን ነው የገለጹት። ሕዝብን እና ልማትን ከሚጎዱ የመከፋፈል ሴራዎች በመውጣት፣ የወንድማማችነት እና የእህትማማችነት ትስስርን ማጠናከር እንደሚገባም አጽዕኖት ሰጥተዋል።
ሰላምን በማስጠበቅ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በጽናት መቀጠል ይገባልም ብለዋል። የመጭው ዓመት የሰላም፣ የብልጽግና፣ የአንድነት እና የዕድገት ዘመን እንዲኾን የሁሉም ትብብር ወሳኝ ነው ያሉት አቶ ጎሹ የጸጥታ ኅይሉ እያደረገ ያለውን ሀገርን የማስቀጠል ተጋድሎ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመላክተዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው የጽናት ቀን ለጸጥታ ኀይሉ ትልቅ ትርጉም ያለው መኾኑን ገልጸዋል። በመከላከያ ሠራዊት፣ በክልሉ እና በከተማዋ የጸጥታ ኀይል የሚከፈለው መሥዋዕትነት የሀገርን ሉዓላዊነት እና ህልውና እያስቀጠለ መኾኑንም ነው ያነሱት።
ቀኑ የሠራዊቱ አባላት ለሀገር እና ለሕዝብ የገቡትን ቃል ኪዳን የሚያድሱበት እና ዓላማቸውን በጽናት የሚገመግሙበት ልዩ ዕለት ነውም ብለዋል። ሠራዊቱ ተራራ ሳይገድበው፣ በዱር በገደል፣ በብርድ እና በቁር ድንጋይ ተንተርሶ ከአባቶቹ ከወረሰው ጀግንነት ጋር ትግሉን አጠናክሮ ቀጥሏል ያሉት ኮማንደር ዋለልኝ የሀገርን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ሕዝብ እና የጸጥታ ኀይሉ በቅንጅት መሥራት እንደሚገባቸውም ነው የገለጹት።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለኝ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
