“በጽናት የተመዘገቡ ድሎቻችንን ማስቀጠል ይገባል” ርእሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ

5
የሐረሪ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ ጳጉሜን ሦሥት የጽናት ቀንን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኢትዮጵያውያን “እኔ” ከሚለው ጠባብ እሳቤ ወጥተው “እኛ ” በሚለው ታላቅ ብሔራዊ የሀገር ግንባታ ራዕይ ሥር በመሰለፍ አንድነታቸውን እና በጽናት የተመዘገቡ ድሎችን ማስቀጠል እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
ቀኑን ስናከብር የሀገርን ሰላም እና ዳር ድንበር ለማስከበር ከፍተኛ መስዋዕትነት ለከፈሉ እና እየከፈሉ ለሚገኙት የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል እና የክልል ፖሊስ አባላት ተገቢውን ክብር እና ምሥጋና በመስጠት ሊኾን እንደሚገባም ገልጸዋል።
በ2018 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ የተመዘገቡት አኩሪ ድሎች የጽናት ማሳያ መኾናቸውን የጠቀሱት ርእሰ መሥተዳድሩ በዓባይ ወንዝ ላይ ፍትሐዊ የመጠቀም መብትን እውን ማድረግ፣ በባሕር በር ዙሪያ በሰላማዊ ዲፕሎማሲ የተገኙ ውጤቶች፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት መጠናቀቁ ዋና ዋናዎቹ መኾናቸውን አንስተዋል።
በክልሉ ሰላምን በማጠናከር ስኬታማ የኮሪደር ልማት፣ የእርሻ እና የማኅበራዊ አገልግሎት ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል። የዓለም ቅርስ የኾነውን ታሪካዊውን የጀጎል ግንብ በቱሪዝም ዘርፍ ለማስተዋወቅ በተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን አብራርተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የመከላከያ፣ የፖሊስ ሠራዊት አባላት እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleለአማራ ሕዝብ የማይናወጥ ማንነቱ ጽናቱ ነው።
Next articleአሱሪቴ፦ የፍቅር እና የአንድነት በዓል