
በኢትዮጵያ የዘመን ቀመር 13ኛዋ ወር ጳጉሜን ወደ አዲስ ዓመት መሸጋገሪያ፤ የዘመን መለወጫ መዳረሻ ድልድይ ናት። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የጳጉሜን ቀናት በተለያዩ ስያሜዎች ታስበው እየዋሉ ነው።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር የጸጥታ መዋቅር የጽናት ቀንን በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ይገኛል።
አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ የጸጥታ ኃይሎች ለየትኛውም ፈተና ሳንበገር የጽናት ተምሳሌት ኾነን በመሥራት ሀገራችንን ከገጠሟት ፈተናዎች ለማላቀቅ እና ክልላችንም የተሟላ ሰላም ባለቤት ለማድረግ የድርሻችንን እየተወጣን እንገኛለን ብለዋል።
ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን የውስጥ እና የውጭ ፈተናዎች በመከላከያ ሠራዊቱ ፊታውራሪነት እና በሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ቅንጅት ማክሸፏንም ጠቁመዋል። ፈተናዎችን ተቋቁመን የሀገራችንን ሰላም ለማረጋገጥ ከወትሮው በላቀ ተነሳሽነት እንሠራለን ነው ያሉት።
የጳጉሜን ሦሥት የጽናት ቀን መከበሩ የጸጥታ ኃይሉን ለበለጠ ግዳጅ የሚያዘጋጅ እና መነቃቃትን የሚፈጥር መኾኑንም ገልጸዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ሰይድ አሊ የደሴ ከተማ የጸጥታ መዋቅር የከተማዋን እና የቀጣናውን ሰላም ለማረጋገጥ ሌት ከቀን እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
የጸጥታ መዋቅሩ ለሀገረ መንግሥት ዘላቂነት እና ለሀገር ሉዓላዊነት መከበር ዋስትና እንደኾነም ገልጸዋል። የከተማዋ የጸጥታ ኃይል የሕዝቡን ሰላም እና ደኅንነት በማረጋገጥ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መኾኑንም አንስተዋል።
የጸጥታ ኃይሉ የሚያደርገው ጥረት እንዲሳካ ኅብተረሰቡ የነበረ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንድያስቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ የጸጥታ ኃይሉ ሀገር የማፍረስ እኩይ አላማን አንግበው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የጸረ ሰላም ኃይሎችን ምኞት በከንቱ ያስቀረ የሀገር መከታ ነው ብለዋል። የከተማዋ የጸጥታ መዋቅር የከተማውን ሰላም በማረጋገጥ ሕዝቡ የልማት ተጠቃሚ እንዲኾን ማስቻሉንም አንስተዋል።
የጸጥታ ኃይሉ በከፈለው መስዋዕትነት በከተማው አስተማማኝ ሰላም በመኖሩ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውንም ገልጸዋል።
#ደሴ #ጳጉሜን_03_2018_ዓ_ም
✍️ ዘጋቢ:- አሊ ይመር
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
