
የኢትዮ ቴሌኮም ሰሜን ምዕራብ ሪጅን በባሕር ዳር ከተማ ለተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
በመርሐ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሙሉዓለም አቤ (ዶ.ር) ኢትዮ ቴሌኮም ለትምህርት ዘርፉ በርካታ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ለትምህርት ጥራት እና ለትምህርት ተሳትፎ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው ብለዋል።
ዛሬ የተደረገው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በአቅም ማነስ ምክንያት መግዛት ለማይችሉ ተማሪዎች ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።
ሕጻናት አዕምሮ ላይ መሥራት ዘላቂ ውጤት ለማምጣት እንደሚያስችል የገለጹት ኀላፊው ድጋፍ የተደረገውን ደብተር በአግባቡ ለተማሪዎች ማድረስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በኢትዮ ቴሌኮም የሰሜን ምዕራብ ሪጅን ኦፕሬሽናል ዳይሬክተር አበበ ጥሩነህ እንደተናገሩት ኢትዮ ቴሌኮም በመላ ሀገሪቱ ለልጆች የትምህርት ቁሳቁሶችን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
ዛሬ ድጋፍ የተደረገው 576 ደርዘን ደብተር መኾኑንም ገልጸዋል። ድጋፉ በትምህርት ቁሳቁስ ችግር ልጆች ከትምህርት ቤት እንዳይቀሩ የማድረግ ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ከትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በተጨማሪ በዲጂታል ቤተ መጽሐፍት ግንባታ እና በሌሎችም ዘርፎች ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
#አሚኮ #BahirDar #EthioTelecom #EducationSupport #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጳጉሜን_03_2018_ዓ_ም
✍️ዘጋቢ:-አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
