
የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ቢሮ ከነሐሴ 28/2018 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 30/2018 ዓ.ም ድረስ “ኤሌክትሮኒክስ መንግሥት ለዲጂታል 2030 መሠረት” በሚል መሪ መልዕክት የዲጂታል መፍትሔዎች ዐውደ ርዕይ እና የፓናል ውይይት በባሕርዳር ከተማ ማካሄዱ ይታወሳል።
ቢሮው የበለጸጉ እና በሥራ ላይ የሚገኙ ችግር ፈች የኾኑ ሲስተሞችን በዐውደ ርዕይ ለጎብኝዎች ክፍት አድርጎ ቆይቷል። ዛሬ ቢሮው የመርሐግብሩን መጠናቀቅ አሥመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ቢሮ ምክትል ኀላፊ የቻለ ይግዛው የክልሉ መንግሥት በ25 ዓመት አሻጋሪ ዕድገት እና ዘላቂ ልማት ላይ ለቴክኖሎጂ ልዩ ትኩረት ሰጥቷል ብለዋል።
ቢሮው ባለፉት ዓመታት ሲያለማቸው እና በየተቋማቱ ተግባራዊ ሲያደርጋቸው የቆያቸውን የዲጂታል መፍትሔዎች በጋራ በማስመረቅ ለሕዝብ ክፍት አድርጎ ቆይቷል ነው ያሉት።
የክልሉ መንግሥት በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያከናወናቸውን ተግባራት ከማሳወቅ ባለፈ ቴክኖሎጂን የመጠቀም ባሕል እንዲያድግ ለማድረግ ታልሞ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ከ35 በላይ የዲጂታል መፍትሔዎች ለምተው ለጎብኝዎች ክፍት ኾነው ቆይተዋል ነው ያሉት። የለሙ ሲስተሞች የሕዝብን አገልግሎት ያሳልጣሉ፤ የመንግሥትን አገልግሎት የመሥጠት አቅም ያሳድጋሉ፤ የዲጂታል ኢኮኖሚን ይደግፋሉ ነው ያሉት።
በመርሐ ግብሩ የክልሉ እና የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች መገኘታቸውን አስታውሰዋል። መርሐ ግብሩ የጋራ ዕውቅና ለመፍጠር እና በጋራ ለመሥራት ዕድል የፈጠረ መኾኑንም ተናግረዋል።
በአገልግሎት ሰጭው እና በአገልግሎት ፈላጊው መካከል ቴክኖሎጂን እንዲያውቅ እና እንዲጠቀም ቁልፍ ዕይታ የፈጠረ መኾኑንም ተናግረዋል። 60 ተቋማት ዐውደ ርዕዩን መጎብኘታቸውንም ገልጸዋል። በቀጣይ በየተቋማቱ ለምተው ለሚተገበሩ የዲጂታል መፍትሔዎች በር የከፈተ ነውም ብለዋል።
የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ባሕልን ለማሳደግ ዕድል የፈጠረ መኾኑንም ገልጸዋል። የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ባሕልን ለማሳደግ እንደሚሠራም አብራርተዋል። የተተገበሩ ሲስተሞችን ወደ ዞን እና ወረዳ ለማውረድ ዕድል የፈጠረ መኾኑንም ጠቁመዋል።
በፖናል ውይይቱ የሳይበር ሴኪውሪቲ፤ የደኅንነት፤ የቴክኖሎጅ ተደራሽነት እና አካታችነት ጉዳዮች ላይ ውይይት መደረጉንም ገልጸዋል። መርሐ ግብሩ ክልሉ በሚቀጥሉት ዓመታት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የኢኮኖሚ ዕድገት ለማረጋገጥ እንደሚሠራ ያሳየበት ነበር ብለዋል።
✅ቢሮው ቴክኖሎጂን ባሕል ለማድረግ ምን ሠራ?
በክልሉ ቴክኖሎጂን ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።
🏢 በክልሉ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በቴክኖሎጂ ታግዞ አገልግሎት እንዲሠጥ ተደርጓል።
👉ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል።
👉 12 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት እንዲኾን እየተሠራ ነው። ለገጠር ነዋሪዎችም ትኩረት ተሠጥቷል።
ቢሮው ጷግሜ 5 “የነገ ቀንን” ቴክኖሎጂን መሠረት በማድረግ በፖናል ውይይት ለማክበር ዝግጅት እያደረገ መኾኑን ተናግረዋል። መርሐ ግብሩ እንዲሳካ ድጋፍ ላደረጉ አካላት በሙሉ ምሥጋና አቅርበዋል።
#አሚኮ #ቴክኖሎጅ #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጳጉሜን_03_2018_ዓ_ም
✍️ዘጋቢ ፦ ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
