
ተራራ ጉልበታቸውን አይፈትነውም፤ ጨለማ ጉዟቸውን አይከለክለውም፤ የበርሃው ሀሩር ከዓላማቸው አያርቃቸውም፤ ዶፍ ዝናብ ጽናታቸውን አይሸረሽረውም፤ በሞት ላይ እየተረማመዱ፤ ጠላትን ድባቅ እየመቱ የሀገራቸውን ሉዓላዊነት ያስከብራሉ እንጂ።
ጽናታቸው ከአለት ይልቅ ይጠነክራል፤ ግርማቸው ከነበልባል እጥፍ ያስፈራራል፤ የክንዳቸው ብርታት እንደ ተራራ ይጠነክራል፤ የግል ጥቅም አያሳስባቸውም፤ ሞት አያሥፈራቸውም በሀገራቸው ሉዓላዊነት፤ ክብር እና አንድነት ላይ የሚመጣ ጠላታቸው ነው።
ደማቸውን አፍስሰው፤ አጥንታቸውን ከስክሰው፤ አካላቸውን አጉድለው የሀገራቸውን ዳር ድንበር፤ ሉዓላዊነት እና ሰላም ያጸናሉ። ጽናትንም በቃል ሳይኾን በተግባር ይገልጣሉ።
ስለ ሀገራቸው ድንጋይ ተንተርሰው፤ በምሽግ ውስጥ ያድራሉ። የጽናት ምሳሌ፤ የጥንካሬ ማሳያ፤ የእውነተኛ የመስዋዕትነት ማሳያ ናቸው የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባለት።
የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገር ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ተዋጊ ጀቶችን፤ ሰው አልባ ድሮኖችን፤ ዘመናዊ ታንኮችን፤ ዘመኑን የሚመጥን ቴክኖሎጂን ከብቁ የሠለጠኑ ባለሙያዎች ጋር አጣምሮ ይዟል።
የሠራዊቱ ጽናት በጦር ሜዳ ብቻ የሚመዘን አይደለም። የሀገርን ሰላም በማስቀጠል፣ የሕዝብን ደኅንነት በማረጋገጥ፣ ሉዓላዊነትን በማስከበር፣ ሀገራዊ ዕድገት እና ልማት በሰላም እንዲቀጥል የሚያስፈልገውን ምቹ ሁኔታ በመፍጠርም በጽናት እየተጓዘ ነው።
ከቀደሙ አባቶች እና እናቶች አልሸነፍ ባይነትን፤ ለክብር እና ሉዓላዊነት መዋደቅን፤ ከራስ በፊት ሀገር ማስቀደምን፤ በጽናት መቆምን ወርሷል።
ሠራዊቱ በየጊዜው የሚገጥመውን ውስጣዊ ፈተና በመቋቋም እና በድል በመሻገር፤ ዘመኑን የሚመጥን ቴክኖሎጂን ከብቁ ሠራዊት ጋር በማጣመር ለዘመናት በጽናት ተጉዟል።
ከኢትዮጵያ አልፎ በቀጣናው ሰላምን ለማጽናት ተሠማርቷል። በባሕር ኀይልም ራሱን አጠናክሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የጽናት ቀንን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያን ስናስብ ሌት ከቀን በጽናት በመቆም ሀገርን ከጠላት ለመጠበቅ ወጥተው ለሚያድሩት ብርቱ የጸጥታ ኀይሎቻችን ቅድሚያ ሳንሰጥ ስለ ሁለንተናዊ ከፍታ ማሰብ ፈጽሞ አይቻልም ብለዋል።
ኢትዮጵያ በራሷ ዕውቀት እና በልጆቿ አቅም የላቀ የቴክኖሎጂ ብቃት ያላቸውን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን፣ ዘመናዊ የታጠቁ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን፣ ከባድ መሣሪያዎችን እና መድፎችን፤ ተተኳሽ ጥይቶችን በራሷ ወታደራዊ ኢንዱስትሪዎች ማምረት ችላለች ነው ያሉት የኢትዮጵያን የመከላከያ ሠራዊት ጽናት በገለጹበት መልዕክት።
#አሚኮ #ጽናት #መከላከያ_ሠራዊት #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጳጉሜን_03_2018_ዓ_ም
✍️ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
