ጽናት፣ ዝግጁነት እና አገልግሎት በደብረ ታቦር !

7

 

​የጽናት ቀን በደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር በወታደራዊ ትርኢት እና በእግር ጉዞ ተከብሯል።

የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር አብራራው አበጀ “የጽናት ቀንን” በማስመልከት የጸጥታ አባላት ያደረጉት ወታደራዊ ትርኢት እና ሰልፍ ከፍተኛ የዲሲፕሊን፣ የሥልጠና እና የሕዝብን ሰላም የማስጠበቅ ዝግጁነታቸውን በግልጽ ያሳየ ነው ብለዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ማረሚያ ቤቶች መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር የቆዬ ዋለ የጸጥታ ኃይሉ ሚና በወታደራዊ ከፍታ እና በዝግጁነት ብቻ የሚወሰን ሳይኾን በችግኝ ተከላ፣ በደም ልገሳ እና ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎችን በማገዝ ረገድም አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

​የጸጥታ ኃይሎቻችን ከአባቶቻቸው የወረሱትን የጽናት፣ የአርቆ አስተዋይነት እና ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ባሕል በኩራት ይዘው የሚቀጥሉ ብቻ ሳይኾኑ አሻፈርኝ የሚልን ጠላት በብቃት የሚያርሙ ብርቱ ክንድ ያላቸው መኾኑን የገለጹት ደግሞ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አመራር የኾኑት ኮሎኔል ሰጥዬ አራጌ ናቸው።

ሠራዊቱ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ጠላቶች የሚመጣን ሴራ በመመከት ሀገሩን በጽናት እያስቀጠለ ያለ የሀገር መከታ መኾኑንም አንስተዋል።

የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር የፖሊስ አባል ምክትል ኢንስፔክተር ገነት ስዩም ፖሊስ ከሕዝብ ጋር ያለውን ጥልቅ ፍቅር እና የልማት አጋርነት እያሳየ የሚገኝ የጽናት ምሳሌ መኾኑን አንስተዋል።

#ደብረ_ታቦር #ጳጉሜን_03_2018_ዓ_ም

✍️ ዘጋቢ፦ ተክለብርሃን ፈንታ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleቴክኖሎጂን በመታጠቅ በጽናት ቁመዋል፤ ሀገርንም አጽንተዋል
Next articleየሰላም አማራጭን መቀበሉ ቀጥሏል።