ኢትዮጵያ የችግር ማሳያነቷ አብቅቶ የጽናት ተምሳሌት ኾናለች” አቶ አገኘሁ ተሻገር

2

 

ጷጉሜን ሦሥት “የጽናት ቀን” በሀገር አቀፍ ደረጃ በታሪካዊው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም እየተከበረ ይገኛል።

በመርሐግብሩ ላይ የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ቀኑ ሀገሪቱ የምትገኝበትን ታሪካዊ እና ፓለቲካዊ ሁኔታ መነሻ በማድረግ የኢትዮጵያን ጽናት በሚያሳይ መልኩ እየተከበረ ይገኛል ብለዋል።

ጽናት ማለት ፈተናን መሻገር፣ መከራ ሲበዛ አብሮ የሚቆም የዕውነተኛ የሀገር ምሰሶ መገለጫ ነው ያሉት አፈ ጉባኤው “እኔ” ከሚለው አስተሳሰብ ወጥተን “ወደ እኛ” የሚለው እና የሀገር ግንባታ መሠረት ወደ ኾነው አስተሳሰብ መሻገር ይገባናል ነው ያሉት።

ሀገሪቱ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የገጥሟትን ፈተናዎች በጽናት ተቋቁማ በርካታ አመርቂ ውጤቶችን በማስመዝገብ ወደ ላቀ ምዕራፍ መሸጋገሯን ገልጸዋል።

2018 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ የተካሄደበት፣ ሕዳሴ ግድብ የተጠናቀቀበት እና በርካታ ፕሮጀክቶች የተጀመሩበት፣ የባሕር በር ጥያቄ የዲፕሎማሲ ድል የተመዘገበበት በመኾኑ ኢትዮጵያ ካሁን በኋላ የችግር ማሳያነቷ አብቅቶ የጽናት ተምሳሌት ኾናለች ነው ያሉት።

የዚህ የማይናወጥ ጉዞ የጽናት ማሳያዎች ደግሞ የጸጥታ እና ደኅንነት ተቋማት ናቸው ያሉት አፈ ጉባኤው ሀገር የመጠበቅ ኀላፊነትን በብቃት በመወጣት ሀገረ መንግሥቱን በማጽናት መስዋዕት እየከፈሉ ላሉ የጸጥታ እና ደኅንነት አባላት ልዩ ክብር መስጠት ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለሕዝቧ መከታ የሚቆሙ ዘመናዊ የጸጥታ ደኅንነት ተቋማትን እየገነባች ያለች የጽናት ተምሳሌት ሀገር ናት። ኢትዮጵያ አሁን ላይ የሕዝቦቿን በጋራ መቆም የሚጠይቅ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች፤ የባሕር በር የማግኘት መብት የማረጋገጥ ጉዞን ለማደናቀፍ የሚሠሩ አካላትን በጋራ ለመመከት ርብርብ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።

የማይናወጥ ሀገራዊ አንድነትን በመገንባት፣ የሳይበር ደኅንነት ብቃትን በማሳደግ እና ዕውቀትን መሠረት ያደረገ የላቀ አቅም መገንባት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በዓሉ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ የብሔራዊ መረጃ ደኀንነት አገልግሎት፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር እና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በጋራ ያዘጋጁት ነው።

#አሚኮ #ጽናት #Ethiopia🇪🇹

#አዲስ_አበባ #ጳጉሜን_03_2018_ዓ_ም

✍️ዘጋቢ ፦ ኢብራሂም መሃመድ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleጽናት ኃይሌን የት አደረሰው?
Next articleየጸጥታ ኃይሉ የጸረ ሰላም ኃይሎችን ምኞት በከንቱ ያስቀረ የሀገር መከታ ነው።