ጽናት ኃይሌን የት አደረሰው?

8

 

“ጽናት” ማለት በቃላት የሚገለጽ የንድፈ ሀሳብ ትርጉም ብቻ ሳይኾን በላብ እና በደም በሚጻፍ የሕይወት ታሪክ ውስጥ የሚበራ ሕያው እውነት ነው።

“ጽናት” መሰናክሎችን እና ተስፋ የሚያስቆርጡ አጋጣሚዎችን ድል የማድረግ ጥበብም ነው።

በኢትዮጵያ የስፖርት እና የቢዝነስ ታሪክ ውስጥ የጽናት፣ የታታሪነት፣ የቆራጥነት እና የአይበገሬነት ሕያው ምልክት ከኾኑት መካከል የ27 ጊዜ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤቱ ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ አንዱ ነው። ሻለቃ አትሌት ኃይሌ የስኬት ማማ ላይ መውጣት በድንገተኛ ዕድል የተገኘ ሳይኾን በትጋት እና በጽናት ጡብ የተገነባ የሕይወት እውነትም ነው።

👉የአትሌቱ ከገጠሯ አሰኮ እርሻ እስከ ዓለም አትሌቲክስ ንጉሥነት !

በ1965 ዓ.ም በአርሲ ዞን አሰላ አቅራቢያ “አሰኮ” በተባለች ገጠር ቀበሌ ከአርሶ አደር ቤተሰብ የተወለደው ሻለቃ አትሌት ኃይሌ እንደማንኛውም የገጠር ልጅ ከብት በማገድ እና ቤተሰቦቹን በእርሻ ሥራ በማገዝ ነበር ያደገው።

እስከ 11ኛ ክፍል በነበረው የትምህርት ዘመኑ ወደ ትምህርት ቤት ረጅም ኪሎ ሜትሮችን በባዶ እግሩ መሮጡ በሩጫው ዓለም ያልታሰበ የሕይወት መንገድ እንደከፈተለት ለመገናኛ ብዙኃን በተደጋጋሚ መግለጹ ይታወሳል።

አትሌቱ የሕይወት አቅጣጫው የተቀየረው በድንገት እንደነበርም ተናግሯል። ገና በ9ኛ ክፍል ተማሪነቱ በሞስኮ ኦሎምፒክ የደመቀውን የአትሌቲክሱን ንጉሥ ምሩጽ ይፍጠርን በምስል መመልከቱ የሕይወቱን አቅጣጫ በፍጹም አስቀየረው። አንድ ቀን በትምህርት ቤቱ ለ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የተዘጋጀ የሩጫ ውድድር መጣ። ኃይሌ የ9ኛ ክፍል ተማሪ በመኾኑ እንዳይወዳደር በመምህራኑ ተከለከለ። ነገር ግን በውስጡ የነበረው ጉጉት እና ሕልም እጁን እንዲሰጥ አልፈቀደለትም።

መምህራኑን አብዝቶ በመለመን እና በመጎትጎት በ1ሺህ 500 ሜትር ውድድር ላይ ለማሟያነት እንዲሳተፍ ተፈቀደለት፤ ውጤቱ ግን የሁሉንም ግምት ያስቀየረ ኾነ። ያልተጠበቀውን ድል በመቀዳጀት የትምህርት ቤቱ መነጋገሪያም ሊኾን ችሏል። ከዚያች ጊዜ ጀምሮ የአትሌቱ ሕልም እና ሕይወት ሙሉ በሙሉ ወደ ሩጫው ዓለም ተቀየረ።

✍️በላብ እና በትጋት የተጻፈ የዓለም የበላይነት

በ1984 ዓ.ም በ18 ዓመቱ በአዲስ አበባ ማራቶን 2 ሰዓት ከ48 ደቂቃ በመግባት አቅሙን ያሳየው ኃይሌ በዚያው ዓመት” በሴኦል” የዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና በ5 ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማሸነፍ የዓለምን ትኩረት ሳበ።

በ1988 (አትላንታ) እና በ1992 (ሲድኒ) ኦሎምፒክ በ10 ሺህ ሜትር ያስመዘገባቸው የወርቅ ሜዳሊያዎች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አድርጓል።

በተለይም በሲድኒ ኦሎምፒክ ከኬንያው ፖል ቴርጋት ጋር ያደረገው የማጠናቀቂያ የሰከንዶች ፍልሚያ በስፖርቱ ታሪክ ውስጥ የጽናት እና የቆራጥነት ትልቁ ማረጋገጫ ኾኖ ተመዝግቧል። ከ1985 እስከ 1991 ዓ.ም በተከታታይ አራት የዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያዎች ባለቤት መኾንም ቻለ።

በዓለም አደባባይ 27 የዓለም ክብረ ወሰኖችን የሰበረው ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ከ800 ሜትር እስከ ማራቶን 61 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብረ ወሰኖችን አስመዝግቧል።

✍️ ይህ የጽናት ውጤት በወርቅ ቀለም የተጻፈ የታሪክ ማህተም ነው።

እነዚህ የክብረ ወሰን ስኬቶች የዕድል ስጦታ ሳይኾኑ የጥብቅ ስነ ምግባር፣ የጽናት እና የዕለት ከዕለት ልፋት ፍሬዎች መኾናቸውን ከባሕር ማዶ እስከ ሀገር ውስጥ ለሚገኙ መገናኛ ብዙኃን በተደጋጋሚ መግለጹ ይታወሳል።

“ለእኔ ማይክሮ ሰከንድ ዋጋ አላት፤ በማይክሮ ሰከንድ ልዩነት 120 ሚሊዮን ብር የሚያስገኝ ዕድል አጥቻለሁ፤ ድል በዕድል ሳይኾን በጽናት እና በብዙ ድካም የሚገኝ የጊዜ ድምር ውጤት ነው፤” በማለትም የስኬቱን ምስጢር አስረግጦ ይናገራል።

✍️ ከሩጫው ሜዳ ወደ ግዙፉ ኢንቨስትመንት !

ሻለቃ ኃይሌ ታሪክ በኦሎምፒክ ስታዲየም ውድድሮች ብቻ አላበቃም። በአንድ ወቅት ከሲኤን ኤን ጋር በነበረው ቃለ መጠይቅ “ስፖርት የሕይወቴ መጀመሪያ እንጂ መድረሻዬ አይደለም” በማለት በኢትዮጵያ በትምህርት፣ በሆቴል፣ በግብርና እና በኢንዱስትሪ ያደረጋቸውን ኢንቨስትመንቶች አብራርቷል።

በሩጫው ያሳየውን ጽናት ወደ ንግዱ ዓለም በማምጣት ዛሬ ላይ ስኬታማ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ባለሀብት ለመሆንም በቅቷል።

አትሌቱ በሩጫው ዓለም በርካታ ወጣቶች አትሌቶች እንዲፈጠሩ አርዓያ ከመኾን ባሻገር በንግዱ ዓለምም በሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል የፈጠረ ግዙፍ ኩባንያ ገንብቷል።

“ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ” መስራቹ ሻለቃ አትሌት ኃይሌ “ታላቁ ሩጫ” የስፖርት ክስተት ብቻ ሳይኾን የሰላም፣ የጤና እና የኢትዮጵያ መልካም ገጽታ ግንባታ መድረክ መኾኑን ገልጿል።

በዓለም የአትሌቲክስ ታሪክ የነገሠው ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ለኢትዮጵያ ኩራት እና ምልክት ነው። ይህ የምንጊዜም የቁርጥ ቀን ልጅ ለሀገሩ በከፈለው መስዋትነት በስሙ መንገድ ተሰይሞለታል፤ መታሰቢያ ሐውልትም ቆሞለታል።

አትሌቱ በአንድ ወቅት የስፖርት እና ሕይወት ፍልስፍናውን አስመልክቶ ለቢቢሲ በሰጠው ቃለ መጠይቅ “የማይቻል ነገር የለም” የሚለውን መርሕ በመጥቀስ ወጣቶች በቁርጠኝነት እና በትጋት ከሠሩ ስኬት ላይ መድረስ እንደሚችሉ አመልክቷል።

ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ለሀገራችን አትሌት ወይም ስኬታማ ነጋዴ ብቻ አይደለም፤ ለጽናት እና ለአይበገሬነት ሕያው ምሳሌ ነው።

እኛም በተሰማራንበት የሕይወት ዘርፍ ሁሉ የሻለቃ አትሌት ኃይሌን ዓይነት ጽናት እና ታታሪነት በመላበስ መሰናክሎችን ወደ ድል በመቀየር ለራሳችንም ኾነ ለሀገራችን አዲስ የብርሃን ምዕራፍ እንክፈት!

#ባሕር_ዳር #ጳጉሜን_03_2018_ዓ_ም

✍️ ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleሀገርን ለማጽናት እስከ መስዋዕትነት።
Next articleኢትዮጵያ የችግር ማሳያነቷ አብቅቶ የጽናት ተምሳሌት ኾናለች” አቶ አገኘሁ ተሻገር