የሰላም ችግኝን ማን ይትከል?

9
🕊️
🕊️ ችግኝ ለመትከል ሆ ብለን ወጣን፤ ለሰላምስ?
ኢትዮጵያውያን ከተባበሩ ምንም የሚገዳቸው ነገር እንደሌለ ማሳያዎች ብዙ ናቸው። ለዚህም ባለፉት ዓመታት የጸጥታ ችግር እንኳ ሳይበግራቸው ያሳኳቸው ትልልቅ ሀገራዊ ስኬቶች ሕያው ምስክሮች ይኾናሉ። ብዙ ጠላት ባለበት እና የውስጥ የጸጥታ ችግር በሞላበት አይነኬ የነበረውን ሕዳሴ ግድብ ሆ ብለው ገድበዋል።
ቅኝ ገዢዎችን ድል በመምታት ዓድዋን የመሰለ በደማቅ ቀለም የተጻፈ ታሪክ ያላቸው ጀግኖች ናቸው። በቅርቡ እንኳ የዓለምን ቀልብ በሳበው የአረንጓዴ አሻራ ሕዝባዊ ርብርብ ሲያደርጉ በውስጥ እና በውጭ የጸጥታ ማዕበሎች ኾነው ክንዳቸው እንዳልዛለ በተግባር አይተናል።
ሚሊዮን ኾነው ወጥተው በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን ተክለዋል። ለዚህም የዓለም ሚዲያዎች ሁሉ በምሳሌነት እያነሱት ነው።
በአንድነት ወጥተው ያሳኳቸው ድሎች ብዙዎች ናቸው።
🕊️ ታዲያ ስለምን መሠረታዊ የኾነውን ሰላም መትከል አልተቻለም ?
ሰላምን መትከል እጅግ ታላቅ እና መሠረታዊ ጉዳይ እንደኾነ ብዙዎች ጽፈዋል፤ ታላላቆች ተናግረዋል፤ ሰላምን ያጡ ሕዝቦችም መሠረታዊነቱን በተግባር አይተዋል። ለዚህም ኢትዮጵያውያን ራሳቸው ምስክሮች ናቸው።
ሰላም ልክ እንደ ትልቅ ዛፍ ሁሉ ሥር ሰዶ፤ ፍሬ አፍርቶ ለሁሉም ጥላ ይኾን ዘንድ መጀመሪያ የሰላም ዘርን መዝራት እና እየኮተኮቱ ማሳደግን እንደሚሻ የሰላም ሚኒስቴር የማኅበራዊ የትስስር ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
🕊️ እናም ስንቶቻችን የሰላም ዘርን እየዘራን ይኾን?
ዓለም ዓቀፍ ዝናን ያተረፉ ታላላቅ ሰዎች ስለሰላም ጥልቅ ሀሳቦቻቸውን አንስተው አልፈዋል። ዛሬም ድረስ የእነሱ ሀሳቦች ይነገራሉ። ያም የኾነው በዘመናቸው መልካም የሰላም ዘርን በመትከላቸው ነው።
ከእነዚህ መካከልም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አሜሪካዊው ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር አንዱ ናቸው። እውነተኛ ሰላም ማለት ፈጽሞ የግጭት አለመኖር ማለት ብቻ ሳይኾን ለተከሰተው ግጭት ፍትሕ ሲሰፍን ማየት ጭምር እንደኾነ እና ከግጭት በኋላ ሰላም ሲያብብ እንደኾነ ይገልጻሉ።
ደቡብ አፍሪካዊው የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ሰላም በምድር ላይ ሊሰፍን የሚችለው አብዝቶ ትዕግስትን እና የጋራ መግባባትን ባሕል ማድረግ ሲቻል ነው ይላሉ።
🕊️ እኛስ የተዛባውን ሰላም እንመልስ ዘንድ ስንቶቻችን ትዕግስትን እና የጋራ መግባባትን አንግበን ይኾን?
የጦርነትን አደገኛነት በመናገር የሚታወቁት 35ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆን ኦፍ ኬኔዲ እኛ ከልብ በመነጨ አኳኋን እና ገብቶን ጦርነትን ማቆም ካልቻልን፤ ጦርነቱ ራሱ እኛን ያቆመናል ብለዋል። ይህም የጦርነትን አውዳሚነት አጽንኦት የሰጡበት ዘመን አይሽሬ ንግግራቸው ነው።
ጆን ጊብሰን “የሰላም ጽንሰ ሀሳብ” በሚለው መጽሐፋቸው የባሩክ ስፒኖዛን ንግግር ዋቢ በማድረግ ሲጽፉ ሰላም ማለት ምንም ጦርነት አለመኖር እንዳልኾነ አስፍረዋል። ይልቁንም ሰላም ከዚያ በዘለለ በጎነትን፣ ቸርነትን፣ ለሰላም ሲባል መልካም መተግበርን ጭምር የሚያካትት እንደኾነ ገልጸዋል።
ሰላም የሁሉ ነገር መሠረት ነው። የትኛውም ነገር መልካም የሚኾነው ሰላም ካለ ብቻ ነው። ልክ እንደምንተነፍሰው አየር ሁሉ ሰላም የመኖራችን ምስጢር ነው፤ ያለ ሰላም ሁሉም ነገር ከንቱ ነው።
🕊️ ታዲያ የሰላም ትርጉሙ የመኖር እና ያለመኖር ጥልቅ ምስጢር ከኾነ ስለምን ለሰላም መዝመት ተሳነን?
ለሰላም ሲባል እኛ ኢትዮጵያውያን አብረን ልንተም ይገባል። ሕዳሴ ግድብን በአንድነት ታሪክ ያደረጉ ክንዶች ሰላም ላይ መጉረፍ አለባቸው።
ለተቀደሰ ዓላማ ችግኝ ለመትከል ጡርንባ ነፍተው የወጡ አንደበቶች ሰላምንም ለማጽናት ማስተጋባት አለባቸው። በሰላም እጦት ያለችው ኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም ይኖራት ዘንድ ታሪክ መሥራት የማይታክታቸው ልጆቿ ሰላምን ፍለጋ ሊማስኑ ይገባል።
የወላድ እናቶች ሲቃ ይቆም ዘንድ ለሰላም ሲባል መዘግየት አያስፈልግም። መጠፋፋት ያከትም ዘንድም ቀጠሮ መያዝ አይገባም። የመጠፋፋት መዘዙ የሁሉም ነውና የሰላም መፍትሔውም ከሁሉም ሊኾን ግድ ይላል። ለጋራ ህልም ሰላም ላይ ማበር፤ ለተረጋጋ ሕይወት የማይጠወልግ የሰላም ችግኝን መትከል ለነገ ይደር አይባልም።
ታሪክ ሠሪ ሕዝቦች በአዲሱ ዓመት ሰላምን ማቀድ አለባቸው። በአዲሱ ዓመት ንጹሕ አየር ይነፍስ ዘንድ የሰላም ጉዳይ ሊገድደን ይገባል፤ ሰላምን ቀዳሚ ተግባር አድርጎ ድርሻን መወጣት፤ ሰላምን ማለም፤ ሰላምን ማቀድ፤ ለሰላም ሆ ብሎ መነሳት ይገባል !
በመረጃ ምንጭነት በዓለም ዙሪያ የሚካሄዱ የሰላም ንግግሮችን በመተንተን የሚታወቀውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (UN
Peacemaker) ድረ ገጽን፣ አፍሪካን ዩኒዬን (African Union) (Peace and Security ) ገጽን እና ሌሎችነም ተጠቅመናል።
✍️ በሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleታሪካዊ መረጃ ሳይጠቀም አደጋዎችን የሚተነብየው ቴክኖሎጂ!