በሀገር አቀፍ ፈተና በሴቶች አንደኛ የኾነችው ተማሪ ሕዳሴ ዘመኑ ሽልማት ተበረከተላት።

18
በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር እንጅባራ ከተማ በሚገኘው አገው ምድር አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በሀገር አቀፍ የ12 ክፍል መልቀቂያ ፈተና 583 ያስመዘገበችው ተማሪ ሕዳሴ ዘመኑ ዕውቅና እና ሽልማት ተበርክቶላታል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክር ቤት ከእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ጋር በመተባበር ባዘጋጀው በዚህ የዕውቅና መርሐ ግብር የላፕቶፕ እና ዘመናዊ ስልክ ሽልማት ተበርክቶላታል።
በመርሐ ግብሩ ተማሪ ሕዳሴ ዘመኑን ለላቀ ውጤት ያበቁ ወላጆቿ እና የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል። የተማረችበት አገው ምድር 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደግሞ የ100ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶለታል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ደስታው ዓለሙ የተማሪ ሕዳሴ ዘመኑ ውጤት የአንድ ቀን ውጤት ሳይኾን የዓመታት የትጋት፣ የትዕግስት እና የቁርጠኝነት ውጤት መኾኑንም ተናግረዋል።
ውጤቱ የሌሎች ተማሪዎችን የእንችላለን መንፈስ የሚያላብስ እና መነሳሳትን የሚፈጥር እንደኾነም አስረድተዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው ስኬቱ የግል ጥረት፣ የመምህራን፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ እና የቤተሰብ ድምር ውጤት መኾኑን ገልጸዋል።
ተማሪ ሕዳሴ ዘመኑ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ያላት ሕልም እንዲሳካ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።
ተማሪ ሕዳሴ ዘመኑ የተደረገላት ሽልማት ለበለጠ ሥራ እንደሚያነሳሳት ተናግራለች።
✍️ ዘጋቢ ፦ሳሙኤል አማረ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየሰላም ችግኝን ማን ይትከል?
Next articleየኃይሌ ማናስ አካዳሚ ካስፈተናቸው ተማሪዎች መካከል 38ቱ የውጭ የትምህርት እድል አገኙ።