“የጀግኖች እናት፣ የአሸናፊነት ምልክት”

6
እርሷ የጀግና ምድር ናት ጀግኖች የሚፈጠሩባት፤ በጀግንነት የሚጠብቋት፤ ጠላቶቿን የሚቀጡላት፤ ክብሯን እና ስሟን ከፍ ከፍ የሚያደርጉላት፤ እርሷ የነጻነት ምድር ናት ቅኝ ገዢ ሁሉ እጅ የሰጠባት፣ እየተሸነፈ የተመለሰባት፤ እርሷ የነጻነት ብርሃን ናት በቅኝ ግዛት ጨለማ የነበረ ሁሉ ብርሃን ያየባት፤ ከጨለማ የወጣባት፤ የነጻነት መንገድን ለማግኘት ብርሃን ያገኘባት፡፡
እርሷ የአሸናፊነት ምልክት ናት ድል ማድረግን የተቸረች፣ ከጥንት እስከ ዛሬ ድረስ በድል የኖረች፤ በአሸናፊነት የደመቀች፤ በግፍ የተነሱባትን ሁሉ የቀጣች፣ የማትጨበጥ እሳት፣ የማትገፋ ተራራ መኾኗን ያስመሰከረች፡፡ እርሷ የአንድነት ምድር ናት በአንድነት የተጠበቀች፤ በልጆቿ አንድነት ነጻነቷን ያጸናች፤ ሉዓላዊነቷን ያስከበረች፣ ከራሷ አልፋ ለጥቁር ዘር ሁሉ አርዓያ የኾነች፣ የነጻነት እናት የተባለች፡፡
እርሷ የማትደፈር ናት ብርቱ ልጆች ያሏት፣ ፈተናዎችን ሁሉ የሚያሻግሯት፤ ጠላቶቿን ሁሉ የሚቀጡላት፡፡ ልጆቿ ቆስለው ያክሟታል፤ ሞተው ያኖሯታል፤ አጥር ኾነው ይጋርዷታል፤ ጋሻ ኾነው ጠላቶቿን ይመክቱላታል፤ ጦር ኾነው ጠላቶቿን ይወጉላታል፡፡
ኢትዮጵያ ከፈተና በላይ የኾነች፣ ከጠላቶቿ ሁሉ የላቀች እና በታሪኳ ለየትኛውም ጠላት ያልተንበረከከች ሀገር ናት፡፡ በየዘመናቱ አያሌ ጠላቶች ተነስተውባታል፤ ነገር ግን ሁሉንም ድል ያደረገች አስደናቂ ናት፡፡ ዛሬም እንደ ትናንቱ ብዙ ጠላቶች አሉባት፡፡ ነገር ግን በልጆቿ ብርታት፣ ጽናት እና አንድነት ሁሉንም ድል ትመታቸዋለች፡፡ እንደ ትናንቱም በአሸናፊነት ትገሰግሳለች፡፡
መንግሥቱ ኃይለማርያም ትግላችን በተሰኘው መጽሐፋቸው ኢትዮጵያ በማንም ጠላት ካልተበገሩ ጥቂት የዓለም ሀገራት መካከል አንደኛዋ ናት ብለው ጽፈዋል፡፡ ኢትዮጵያ በጀግኖቿ የአርበኝነት ተጋድሎዋ በነፃነት መኖር ብቻ ሳይኾን በዓለም የታፈረች እና የተከበረች ናት ይላሉ።
የኢትዮጵያ መልካ ምድራዊ አቀማመጥ፣ ለም አፈሯ፣ ድንግል የተፈጥሮ ሀብቷ፣ ንፁሕ እና ነፋሻ አየሯ ከጥንታዊዎቹ ኃያላን ግሪኮች እና ከሮማውያን ምኞት እና ሙከራ ሌላ በየጊዜው ኃይል የተሰማቸው፣ የቅኝ ግዛት ምኞት ያሰከራቸው ወራሪዎች እና ተስፋፊ ጠላቶቿ ኢላማ አድርገዋታል፡፡ ከፊሉ ቅኝ ግዛታቸው ሊያደርጉን፣ የተቀሩት ለመስፋፋት ሞክረው ሁሉም እየተቀጡ ተመልሰዋል ነው የሚሉት፡፡
የኢትዮጵያ ጀግኖች አይበገሬ የአርበኝነት ተጋድሎ ገድል የሚያስረዳን አንድነት ኃይል መኾኑን፤ አንድነት ታላቅነት መኾኑን ነው። የዚህች የጥንታዊት አይበገሬ አኩሪ ሀገር ባለቤት ለመኾን የቻልነው በአንድነታችን እና በኅብረታችን ነው ይላሉ። ከጥንት ጀምሮ የየዘመኑ ተከታታይ ትውልዶች በፈረቃ እና ባላቋረጠ መሪር መስዋዕትነት ያቆዩንን ሀገር እና ያወረሱንን አኩሪ የታሪክ ቅርስ እኛም በፈንታችን ለተከታዩ ትውልድ እናወርሳለን ወይስ እናፈርሳለን ብሎ የዛሬው ትውልድ ራሱን መጠየቅ አለበት ነው የሚሉት፡፡
ይህች ጥንታዊት እና ጀግና ሀገር ዛሬም በዙሪያ ገባው የሚያሰፈስፉባትን የውጭ እና የውስጥ ጠላቶች ድል ማድረግ የሚችሉ ልጆች አሏት፡፡
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ለኢትዮጵያ ክብር እና ሉዓላዊነት ተዋድቀው ሀገር ያቆዩን አያቶቻችን በእኛ ዘመን ያለው ዕድል አልነበራቸውም፤ ከሰማይ የመርዝ ዝናብ እየዘነበባቸው በጎራዴ እና በዲሞፍተር ኢትዮጵያን ከቅኝ መገዛት ተከላክለው እና አንድነቷን ጠብቀው አስረክበውናል ብለዋል፡፡
ዛሬ የቴክኖሎጂ ግኝነቶችን የታጠቅንበት፣ የሰው ኪሣራ ቀንሰን በነበልባል አቅም የምንዋጋበት አቅም ላይ እንገኛለን፤ ዘመናዊ መሣሪያ ሳይታጠቁ ሀገር ያስረከቡን አያቶቻችን አጥንት እንዳይወጋን ባገኘነው ዕድል ተጠቅመን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር መታገል አለብን ነው ያሉት፡፡
ታሪካዊ እና ወቅታዊ ጠላቶቻችን ኢትዮጵያን ከምሥራቅ አፍሪካ ካርታ ላይ ለማጥፋት ቢሞክሩም አልቻሉም፤ በዚህ ዘመን ለመምጣት ቢሞክሩም ኢትዮጵያን አይችሏትም፤ ነገር ግን በባንዳዎች አማካኝነት ኢትዮጵያን እየሞከሯት ነው፣ ስደተኛ እና ሰርጎ ገብ ባንዳ የራሱን ሀገር አደጋ ላይ ለመጣል እየሠራ ነው ብለዋል፡፡
‌መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያ ምሽግ እና መከታ ነው፤ ሠራዊቱ ሀገር ለማፍረስ የሚተጉ ጽንፈኞችን እና ነውጠኞችን እየመከተ መኾኑንም ተናግረዋል።
ከሁሉም በፊት ሀገር ይቀድማል፤ ሥልጣንም ኾነ ፖለቲካ ከሀገር ሕልውና ጋር የማይገዳደር መኾን ይገባዋል ነው ያሉት፡፡ ሀገራችንን እናፈርሳለን የሚሉትን እንመክታለን፣ ሀገር እናጸናለን፣ ለልጆቻችንም እናስተላልፋለን ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያን ልጆቿ ይጠብቋታል፤ አስከብረውም ያኖሯታል፤ ጠላቶቿንም ይቀጡላታል።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleጽንፈኝነት የሕዝብ እና የሀገር ጠንቅ ነው።
Next articleበአዲስ አበባ ከተማ አራት ዘመናዊ የትራንስፖርት ተርሚናሎች ተገንብተው ወደ ሥራ ገቡ።