
በከተሞች የትራፊክ መጨናነቅን መቀነስ እና የመጓጓዣ ሥርዓቱን ማዘመን ለነዋሪዎች ምቹ እና ዘመናዊ ከተማን ከመፍጠር አንጻር ወሳኝ ነው።
በአዲስ አበባ አዲስ የተገነቡት ዘመናዊ የትራንስፖርት ተርሚናሎችም የከተማዋን የትራንስፖርት ፍሰት በማቀናጀት ምቹ እና ዘመናዊ ከተማ ለመፍጠር የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ መኾኑን የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
የከተማ አሥተዳደሩ አራት ዘመናዊ የትራንስፖርት ተርሚናሎችን ገንብቶ ሥራ መጀመራቸውን ያሳወቁት ከንቲባዋ ጎተራ፣ ቦሌ፣ የካ እና ቀበና የተቀናጀ የትራንስፖርት ተርሚናል እና የገበያ ማዕከላት ዛሬ ተመርቀው ሥራ ጀምረዋል።
ተርሚናሎቹ የሕዝብ ትራንስፖርትን በአንድ ሥርዓት በማስተባበር፣ የመነሻ እና መድረሻ ነጥቦችን በማደራጀት የትራፊክ ፍሰቱን ለማሳለጥ እንደሚያግዙ ተናግረዋል።
ይህም በከተማዋ የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅ፣ የሕዝብ ትራንስፖርት መበታተን እና በመንገድ ዳር የሚፈጠረውን ጫና ለመቀነስ የሚያግዝ ነው።
በተርሚናሎቹ የተገነቡ ፕላዛዎች፣ ፓርኪንጎች እና ሱቆች የነዋሪዎችን አገልግሎት የሚያሳልጡ እና የአኗኗር ምቾትን የሚያሻሽሉ መኾናቸውንም ከንቲባዋ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቶቹ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ሲኾን የከተማዋ ነዋሪዎችም የተሻለ እና ምቹ አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጋሉ።
ተርሚናሎቹ የአረንጓዴ ትራንስፖርት ራዕይን ለማሳካት የሚያግዙ የባትሪ መሙያ ጣቢያዎችን የያዙ ሲኾን ማኅበራዊ መስተጋብርንም ለማጠናከር የሚያግዙ ናቸው።
በተጨማሪም ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያግዙ የደኅንነት ሥርዓት የተዘረጋላቸው እና ዘመናዊነትን የጠበቁ መሠረተ ልማቶች ናቸው።
ከ20 ሺህ በላይ ወጣቶች በፓርኪንግ ሥራ መሰማራታቸውን የገለጹት ከንቲባ አዳነች አበቤ ከተማዋ ለሰው ልጅ ክብር የሚመጥኑ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት ለዜጎቿ ምቹ መኾን እንዳለባት ገልጸዋል።
የአካባቢው ማኅበረሰብ የተገነቡትን የመሠረተ ልማቶች በመንከባከብ እና በመጠበቅ ተጠቃሚ እንዲኾንም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ አየለ መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
