
ከትምህርት ጋር የረጅም ዘመናት ትስስር ባለው በአማራ ክልል ሕዝብ ዘንድ ዕውቀት ከማኅበራዊ ክብር እና ከሀገር ፍቅር ጋር በጥብቅ ይቆራኛል። ዕውቀት የሰው ልጅ መለኪያ፣ መለያ እና መገለጫ ተደርጎም ይቆጠራል።
ታዲያ ዕውቀትን ከሕይወት ልምድ ባለፈ በትምህርት እንደሚገኝ ተቀብሎ ከጥንት ጀምሮ እስከአሁን በቤተ ክህነት እና በመስጊድ ትውልድን የስብዕና እና የሞራል ባለቤት ሲያደርግ ኖሯል።
ልጅን በዘመናዊ ትምህርት አሳልፎ ትልቅ ደረጃ ማድረስ ዛሬም ድረስ እንደ ትልቅ የሕይወት ዘመን ስኬት ተደርጎ ይቆጠራል።
የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ፤ መሬት እየጠበበ እና የኑሮ ጫና እየከበደ በመጣበት በዚህ ወቅት ትምህርት እንደ አንድ የድህነት መውጫ በር ተደርጎ ይታያል። ለዚህም ነው “እኔ የኖርኩበትን ሕይወት ልጄ ሊኖርበት አይገባም፥ የተሻለ ኑሮ ይገበዋል” በሚል ጽኑ እምነት ከሚበላው ቀንሶ እና ጥሪቱን አሟጥጦ ልጁን የሚያስተምረው።
የኑሮ ጫና እና የትምህርት ፈተና
በጊዜ ሂደት ግን የትምህርት ቁሳቁስ ዋጋ እየጨመረ መጣ። ዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅም ያላቸው እና ብዙ ልጆችን የሚያስተምሩ ወላጆች ቁሳቁሱን አሟልተው ልጅን ማስተማር ፈተና ሲኾንባቸው ታዬ። ይህ ዓይነቱ ክፍተት በሕጻናት ላይ የሥነ ልቦና ጫና የሚፈጥር፣ ውሎ አድሮ ከትምህርት ራሳቸውን እንዲያገሉ የሚያደርግ እና ለክልሉ መማር ማስተማር ሂደት ዋነኛ እንቅፋት ኾኖም ተገኘ።
“አንድም ሕጻን ከትምህርት ገበታ መቅረት የለበትም” 
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ “አንድም ሕጻን በትምህርት ቁሳቁስ ችግር ከትምህርት ገበታ መቅረት የለበትም” በሚል መሪ መልዕክት ለሕጻናት ቁሳቁስ የማሟላት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ንቅናቄ ሲከናወን ቆይቷል። ንቅናቄው ዘንድሮም በከፍተኛ ርብርብ ቀጥሏል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ መኳንንት አደመ እንደገለጹት ተማሪዎች በቁሳቁስ እጥረት ከትምህርታቸው እንዳይደናቀፉ ውጤታማ ሥራ ተከናውኗል።
እስከ ነሐሴ 13/2018 ዓ.ም ከ234 ሺህ በላይ ደርዘን ደብተር፤ ከ29 ሺህ በላይ ፓኮ እስክርቢቶ እና ሌሎች በርካታ አስፈላጊ የትምህርት ግብዓቶች ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሠብሥቦ ለተማሪዎች ተሰራጭቷል። ይህ ሀብት በገንዘብ ሲሰላ በመቶ ሚሊዮኖች ብር ይገመታል።
የታሪክ አሻራ 
ታዲያ የተደረገው ሕዝባዊ ርብርብ ከቁጥር በላይ ከፍተኛ ጠቀሜታን ያስገኘ ኾኗል። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሕጻናትን ከሥነ ልቦና ጫና በማላቀቅ እና በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሕጻናትን ወደ ትምህርት ገበታ በመመለስ ከትምህርት እንዳይርቁ፤ ከተስፋቸው እንዳይቀሩም አድርጓል።
ርብርቡ ለክልሉ መማር ማስተማር ውጤታማነት እና የትምህርት ጥራት መሻሻል ከፍተኛ አበርክቶ እያደረገ ይገኛል። በ2019 የትምህርት ዘመን በክልሉ መዝግቦ ለማስተማር የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ትልቅ እገዛ እያደረገ መኾኑም ተመላክቷል።
ይህ ሰፊ የሕዝብ ትብብር በኢትዮጵያ ታሪክ ዘመናዊ ትምህርትን ለማስቀጠል የተገኘ ታላቅ አርዓያነት ያለው መፍትሔ ኾኖም ይመዘገባል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
