
የኢትዮጵያ እና የቀይ ባሕር ግንኙነት በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታትን ያስቆጠረ ጥልቅ ታሪካዊ፣ ጂኦፖለቲካዊ እና የንግድ ትስስርን የያዘ ነው።
ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ የወጭ ንግድ በር፣ ከቀደምት ሥልጣኔዎች ጋር የሚያገናኛት ድልድይ፣ የሉዓላዊነቷ እና የደኅንነቷ ወሳኝ አካል ኾኖ ኖሯል።
በወቅቱ ጠንካራ የንግድ የበላይነትን በመያዝ ዝናዋን ለዓለም አሠራጭታለች። ዓለም አቀፍ የንግድ ማዕከልም አድርጓት እንደነበር ታሪክ ያስረዳል። ነገር ግን ይህ ታሪካዊ ክብሯ እና የጂኦግራፊያዊ ጸጋዋ ላለፉት ዘመናት ከውጭ እና ከውስጥም በተሰነዘሩ ስልታዊ የሴራ ሸርጦች ሃብቷን እንድታጣ አስገድዷቷል። ይህም በኢኮኖሚዋ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮባታል።
የተከዜ ፖለቲካ መጽሐፍ ጸሐፊ ቹቹ አለባቸው (ዶ.ር) ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ በተፈጥሮ የተሠጠ አንጡራ ሃብቷ መኾኑን ይገልጻሉ። በአክሱም ዘመነ መንግሥት በምጽዋ አካባቢ አዱሊስን በመጠቀም ዓለም አቀፍ የንግድ ማዕከል ካደረጓት ምክንያቶች አንዱ የቀይ ባሕር መኾኑን አውስተዋል። በወቅቱ ሀገሪቱ የዓለም ሥልጣኔ ባለቤት እንደነበረች ነው የተናገሩት።
ከዚያን ጊዜ በኋላ የባሕር በር ስታገኝ እና ስታጣ ቆይታለች ብለዋል።
በታሪክ አጋጣሚዎች የሀገሪቱ ሁኔታ እየተለዋወጠ ሲመጣ፣ ጠንካራ በነበረችበት ጊዜ የባሕር በሯን ጠብቃ ለሰላም፣ ለደኅንነት እና ለልማት ስትጠቀምበት፤ ስትዳከም ደግሞ ከባሕር በር እየራቀች እና ባዕዳን እየወረሯት ከጥቅሟ ተነፍጋለች ነው ያሉት። ተፈጥሯዊ ሃብቷን እንድታጣም ተደርጓል።
በተለይም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብቻ ሳይኾን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለነጭ ቅኝ ገዢዎች ያልተንበረከከች ብቸኛ የነጻነት ምልክት መኾኗ የውጭ ኃይሎችን ቀልብ ስቧል። የቅናት መንፈስ አድሮባቸዋል። በዚህም ኢትዮጵያ፣ በውጭ ኃይሎች የረጅም ጊዜ የፖለቲካ ሴራዎች ምክንያት ከባሕር ከባቢዋ እንድትርቅ መደረጉንም ያስረዳሉ። ሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድንም የውጭ ኅይሎችን ሴራዎች በመተግበር ሀገሪቱ የባሕር በር አልባ እንድትኾን ተፈርዶባታል ብለዋል።
ይህም ተፈጥሯዊ እስትንፋስ የኾነውን የባሕር በር በማጣቷ ኢትዮጵያ በዓመት ከ2 ቢሊዮን በላይ የአሜሪካ ዶላር ለወደብ ኪራይ እንደምታወጣ መረጃዎች ይጠቁማሉ ነው ያሉት። ይህ ከፍተኛ ወጪ የሀገሪቱን የወጭ ንግድ እና ኢኮኖሚ በእጅጉ እየፈተነው ይገኛል። የሕዝብ ቁጥር እያደገ እና ኢኮኖሚው እየሰፋ ባለበት በዚህ ወቅት ከባሕር በር ርቆ መኖር የሕልውና ጉዳይ መኾኑንም አንስተዋል።
ቹቹ አለባቸው (ዶ.ር) ሀገሪቱ ከባሕር በር መራቋ የኢኮኖሚ፣ የደኅንነት እና የጂኦፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በእጅጉ አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ተናግረዋል። ለዚህም እንደ ተከዜ ተፋሰስ እና የወልቃይት አካባቢ ያሉት ስፍራዎች ለጂኦስትራቴጂክ ደኅንነት እና ሁለንተናዊ ትስስር እጅግ ወሳኝ ናቸው በለዋል። በዚህም የቀይ ባሕር የባለቤትነት ጥያቄ የሀገሪቱ የደም ሥር እና ከባሕር በር ርቆ መኖር ፈጽሞ የማይታሰብ መኾኑንም ገልጸዋል።
የባሕር በር ባለቤት ለመኾን ሕዝቡ፣ ምሁራን እና ሌሎችም አካላት ጋር በቅንጅት ጽኑ አጀንዳ መያዝ ይገባል። የህልውና ጉዳይ መኾኑንም በመገንዘብ በሀገር አቀፍ ደረጃ ጠንካራ አቋም መያዝ፤ ዓለም አቀፍ ልምዶችን እና የ”ሰጥቶ መቀበል” መርህን በመከተል፤ በሰላማዊ መንገድ እና በዲፕሎማሲያዊ ውይይቶች ጥረቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ነው ያስረዱት።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መኾኗ ሰላሟን እና ሉዓላዊነቷን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከፍ ያለ ፋይዳ አለው። በተለይም የኢኮኖሚ ዕድገቷን ለማፋጠን ከስትራቴጂካዊ ጉዳዮች አንዱ ተደርጎ ይወሰዳል ነው ያሉት።
የባሕር በር ማግኘት የቅንጦት ጥያቄ ሳይኾን፣ የኢኮኖሚ ደኅንነትን ለማረጋገጥ እና የወደፊት ዕጣ ፈንታን በራስ አቅም ለመወሰን የሚደረግ የሕልውና ትግል መኾኑም ተመላክቷል።
በሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
