“አማራ ክልል በልማት ተወዳዳሪ እንዲኾን በሁሉም ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

13
የአማራ ክልል መንግሥት የክልሉን የ2018 በጀት ዓመት የአሻጋሪ ዕድገት እና ዘላቂ የልማት ዕቅድ አፈጻጸም በተመለከተ ግምገማ ማካሄድ ጀምሯል።
በመድረኩ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ እንዲኹም የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይን ጨምሮ ሌሎችም የክልሉ መሪዎች ተገኝተዋል።
በመክፈቻ መርሐ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የ2018 በጀት ዓመት ቀደም ሲል የተዘጋጀውን የአምሥት ዓመታት የስትራቴጅክ ዕቅድ መተግበር የጀመርንበት ነው ብለዋል።
የተዘጋጀው ዕቅድ በበጀት ዓመቱ ከንድፈ ሀሳብ አልፎ የተሻለ አፈጻጸም የታየበት እና ተግባራዊ ውጤት የተመዘገበበት መኾኑን ተናግረዋል።
አማራ ክልል በልማት ተወዳዳሪ እንዲኾን በሁሉም ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባልም ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ።
ለዚህም በሰው ሃብት ልማት፣ በተቋም ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ ልማት፣ ሰላም እና ደኅንነትን በማረጋገጥ በኩል በዕቅድ ላይ የተመሠረተ የጋራ አቅጣጫን መከተል እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
የጋራ ግንዛቤ ለጋራ ጉዞ እና ስኬት መነሻ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ከታለመው ርዕይ ለመድረስ ተቋማት እና መሪዎች በጋራ ኀላፊነት እንዲሠሩም አሳስበዋል።
በመርሐ ግብሩ በ2018 በጀት ዓመት የአሻጋሪ ዕድገት እና ዘላቂ ልማት ዕቅድ አፈፃፀም በጥልቀት እንደሚገመገም ይጠበቃል።
በተጨማሪም የክልሉ የ2019 በጀት ዓመት የአሻጋሪ ዕድገት እና ዘላቂ ልማት ዕቅድ ትውውቅ እንደሚደረግም የተያዘው መርሐ ግብር ያመላክታል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየሰላም አማራጭን መጠቀም ለሕዝብ ሰላም መቆም ነው።
Next articleከአዱሊስ እስከ ዛሬ፦ ኢትዮጵያ እና ቀይ ባሕር