የሰላም አማራጭን መጠቀም ለሕዝብ ሰላም መቆም ነው።

14
ጦርነት ሁልጊዜም ዋጋው ከባድ ነው። በግንባር የሚረግፉት ወጣቶች፣ የሚያለቅሱ እናቶች እና የሚፈናቀሉ ንጹሐን የአንድ ሀገር እና ሕዝብ አካል ናቸው። የሰላምን አስፈላጊነት ከጦርነቱ ማዕበል ውስጥ ከነበሩት ሰዎች አንደበት መስማት ደግሞ የእውነቱን ጥልቀት አጉልቶ ያሳየዋል።
በአማራ ክልል በትጥቅ ትግል ሲንቀሳቀሱ የነበሩት እና አሁን ላይ ወደ ሰላማዊ ትግል የተመለሱት ኢያሱ አባተ ከአሁን በፊት በሰጡት ማብራሪያ የትጥቅ ትግሉ በብዙ ወጣቶች ዘንድ ሕዝብን የሚጠቅም መስሎ ቢታይም በተግባር ግን የታወረ የግል እና የቡድን የሥልጣን ፍላጎትን ለማሳካት የሚደረግ እንቅስቃሴ መኾኑን ገልጸዋል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ ጫካ የገባው ታጣቂ ኅይል የራሱን ጥቅም ከማሳደድ ውጭ በፍጹም ለአማራ ሕዝብ ጥቅም የሚታገል አይደለም ብለዋል።
የትጥቅ ትግሉ ሕዝብን የሚጠቅም ያለመ መስሎት እና ያልገባው ብዙ ወጣት በቡድኑ ውስጥ እንዳለም ገልጸዋል። የሚያሳዝነው ግን ዓላማ በሌለው ጦርነት ብዙ ወንድሞቻችን ሳይገባቸው ሕይወታቸውን ገብረዋል ነው ያሉት።
የትጥቅ ትግሉ በተለያየ መንገድ ያልተገኘውን የሥልጣን ፍላጎት በአማራ ሕዝብ ጥያቄ ስም ለማሳካት ያለመ መኾኑንም አንስተዋል። የአማራን ሕዝብ ለማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ ልቦናዊ ቀውስ መዳረጉንም ገልጸዋል።
ይህ ኃይል በዚህ ከቀጠለ ለአማራ ሕዝብ ዕዳ እንጅ ተስፋ የለውም ብለዋል። ከዚህ በላይ ከሄደ የአማራን ሕዝብ መከራ እና ሰቆቃ ከማራዘም ውጭ የሚፈይደው ነገር አለመኖሩንም ተናግረዋል።
ታጣቂ ቡድኑ “ነጻ ያልወጣ ነጻ አውጭ ነው ቢባል ይገልጸዋል፤ ምክንያቱም ንጹሐንን ከመግደል፤ እርስ በርስ ከመገዳደል፤ ከግል ጥቅም እና ከሥልጣን ፍላጎት ነጻ ያልወጣ በሕወሃት እና በሻቢያ ረጅም እጆች የታሰረ ነው” በማለትም የቡድኑን ውድቀት አብራርተዋል።
“ታጣቂ ኃይሉ ላለፉት ሦሥት ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው ጥቁር ጠባሳ አሳርፏል፤ በዚህ ሦሥት ዓመት ውስጥ ያልተነገረ እንጅ ያልተደረገ የለም” በማለትም የድርጊቱን አስከፊነት ገልጸውታል።
ታጣቂ ቡድኑ ንጹሐንን ከመግደል እና እርስ በርስ ከመገዳደል ያልተሻገረ ከመኾኑም በላይ እናቶችን የማስገደድ፣ ካህናትን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን እና መምህራንን በአደባባይ የመግደል አስከፊ ድርጊቶች መፈጸሙን ተናግረዋል።
እነዚህ አካላት በአማራ ሕዝብ ስም እየማሉ በሚሊዮን ገንዘብ የሚያካብቱ እና በእጅ አዙር ፋብሪካዎችን የሚከፍቱ መኾናቸውን አንስተዋል።
በብዙዎች ዘንድ የሕዝብ ጥያቄ መስሎ የተጀመረው ትግል አሁን ላይ በዘረፋ፣ በደጋፊ ዲያስፖራ እና በውጭ ኃይሎች የሚደጎም የግል ጥቅም ማካበቻ መኾኑንም አንስተዋል። ይህ ጥቅም እንዳይቋረጥባቸው ትርጉም የለሽ የጫካ ትግሉን ማስቀጠል እና ማራዘም ነው የሚፈልጉት ብለዋል።
ቡድኑ የሕዝብ ድጋፍ ለማግኘት ሃይማኖትን እንደ ፖለቲካ መጠቀሚያ ማድረጉ የአስተሳሰብ ግብዝነትን የሚያሳይ እና የሕዝቡን የሞራል እና የባሕል እሴት ያሳነሰ መኾኑን ገልጸዋል።
በርካታ ታጣቂዎች የትግሉን አቅጣጫ በመረዳት የሰላም አማራጭን በመቀበል ወደ ኅብረተሰቡ ተቀላቅለዋል።
አሁንም በጫካ የሚገኘው እና ያልገባው ወጣት ይህንን እውነት ተረድቶ የእርስ በርስ እልቂቱን እንዲያቆም፣ ጥያቄውን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት እጁን ለሰላም እንዲዘረጋ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleሰላምን መቼ ነው የምናቅደው?
Next article“አማራ ክልል በልማት ተወዳዳሪ እንዲኾን በሁሉም ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ